ሩሲያ የኒውክሌር መሳሪያዎቿ ላይ አሜሪካ ፍተሻ እንዳታደርግ አገደች

የሩሲያ አር ኤስ 24 ያርስ ስትራቴጂክ የኒኩለር ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ሩሲያ 'ስታርት' ተብሎ በሚታወቀው ስምምነት መሰረት አሜሪካ በስትራቴጅያዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿ ላይ የምታደርገውን ፍተሻ "ለጊዜው" ማገዷን አስታወቀች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሜሪካ እየተጠቀመችብን ነው ባለውና፣ ሩሲያ በአሜሪካ ግዛት ውስጥ የምታደርገውን ተመሳሳይ የፍተሻ መብቷን በመንፈጓ መሰል እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል።

አሜሪካ በበኩሏ የዩክሬን ወረራን ተከትሎ በሩሲያ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች በአገራቱ መካከል ያለውን ሁኔታ ቀይሯል ብሏል።

ሁለቱ አገራት የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎቻቸውን በተመለከተ ፍተሻዎችን የሚያደርጉበትን ስምምነት እኤአ በ2011 ነበር ተግባራዊ የሆነው።

ስታርት በቀድሞ የቀዝቃዛ ጦርነት ተቀናቃኞች አሜሪካ እና ሩሲያ መካከል ተግባራዊ እየተደረገ ያለ የመጨረሻው የጦር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነት ነው።

ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ሊያሰማሩ የሚችሉትን የረዥም ርቀት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ 1,550 ላይ የገደበ ስምምነት ነው።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እገዳው የተላለፈው በስምምነቱ ላይ በተቀመጠው "ልዩ ሁኔታዎች" መሰረት ነው ብሏል።

እገዳው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር አዲስ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ስምምነት ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ከገለጹ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው። አሁን በሥራ ላይ ያለው ስምምነት እኤአ 2026 የሥራ ጊዜው ያበቃል።

ሚኒስቴሩ አሜሪካ የአየር ግንኙነትን ማቋረጥን የመሳሰሉ "ከዚህ ቀደም የነበሩ እውነታዎችን" ወደ ጎን ብለላች ሲሉ ከሰዋል።

የስታርት ስምምነት በቀድሞዋ ሲቪየት ኅብረት እና አሜሪካ መካከል ለዓመታት የተካሄዱ የኒውክሌር ጦርነትን ለማስቀረት ያለሙ የጦር መሳሪያ ቅነሳ ንግግር ተከትሎ ነበር የጸደቀው።

ሩሲያ በየካቲት ወር ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች ግጭቱ ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊሸጋገር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መስጠትን ጨምሮ፣ ጠብ አጫሪ ፕሮፖጋንዳዎች ሲሰሙ ቆይተዋል።

በአንዳንድ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሩሲያ ከኔቶ ጋር ውጥረት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ተንታኞች ስለሞስኮ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፉክክር አዘል ንግግሮችን ሲያደርጉ ተደምጠዋል።