ትራምፕ በርካቶች በተገኙበት የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ ቻርሊ ከርክን "የአሜሪካ ጀግና" ሲሉ አወደሱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለታዋቂው አሜሪካዊ ወግ አጥባቂ አክቲቪስት ቻርሊ ከርክ በአሪዞና በተዘጋጀ መታሰቢያ ላይ ተገኝተው ከርክን "ታላቁ የአሜሪካ ጀግና" እንዲሁም "ሰማዕት" ሲሉ አወደሱ።

እሁድ ዕለት በተካሄደው የቻርሊ ከርክ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ ትራምፕ ዋነኛ ተናጋሪ የነበሩ ሲሆን ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹማምንት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ትራምፕ "ከርክ የተገደለው በጀግንነት ስለኖረ ነው።በድፍረት ኖሯል፤ እንዲሁም ጥሩ አድርጎ ተከራክሯል" ሲሉ በስታዲየም ውስጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ተናግረዋል።

የከርክ ባለቤት ኤሪካ በእንባ ታጅባ ንግግር ያደረገች ሲሆን በባለቤቷ ግድያ የተጠረጠረውን ግለሰብ ይቅርታ እንዳደረገችለት ገልጻለች።

"ባለቤቴ ቻርሊ ወጣቶችን ማዳን ነበር የሚፈልገው፤ ልክ ሕይወቱን እንደቀጠፈው ያለውን ወጣት" ስትል አክላለች።

"ይቅር ብየዋለሁ፤ ክርስቶስ ያደረገው ያንን ነው። ለጥላቻ መልሱ ጥላቻ አይደለም።" ብላለች ኤሪካ።

የመታሰቢያ ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት በስታዲየሙ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰልፈው የተወሰኑ ደግሞ በአካባቢው አነስተኛ ድንኳን ጥለው ተቀምጠው የዝግጅቱን መጀመር ሲጠባበቁ ነበር።

አብዛኞቹ አሜሪካን ዳግም ትልቅ እናደርጋታለን (MAGA) የሚል ኮፍያ አድርገው የነበረ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የታተሙትን ቀይ፣ ነጭ እና ሰማያዊ አልባሳት ለብሰው ተገኝተዋል።

በስታዲየሙ ውስጥ የፖለቲካ ቅስቀሳ ወይንም የትልቅ ቤተ እምነት የአምልኮ ሥርዓት የሚካሄድ ይመስል ነበር።

በስታዲየሙ 10ሺህ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ዘማሪያን መዝሙሮቻቸውን አቅርበዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከርክ ከሌሎች ጋር በመሆን ከመሰረተው 'ተርኒንግ ፖይንት ዩኤስኤ' ድርጅት የመጡ እንዲሁም በወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚታወቁ ግለሰቦች፣ የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ በከርክ ሥራ ሕይወታቸው መለወጡን የሚመሰክሩ ሰዎች ንግግር አድርገዋል።

ሁሉም በንግግራቸው ላይ የ31 ዓመቱ ከርክ የጀመረውን የአክቲቪዝም ሥራ የማስቀጠል አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን ሁሉም ለሥራው የነበረውን ጥልቅ እምነት አንስተዋል።

ከርክ በተተኮሰበት ወቅት በዩታ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ሲከራከር የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ ሰማዕት መሆኑ እንዲሁም በወግ አጥባቂዎች እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ ታሪካዊ አርዓያ ሰብ እንደሚታይ ሲገለጽ ነበር።

በቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረው ታይለር ሮቢንሰን በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ ተመስርቶበታል።

በታዋቂው አሜሪካዊ ወግ አጥባቂ አክቲቪስት ቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረው ታይለር ሮቢንሰን እስካሁን ድረስ ግድያውን መፈጸሙን ለፖሊስ ባያምንም ከጓደኛው ጋር የተለዋወጣቸው መልዕክቶች ላይ ግን ወንጀሉን መፈጸሙን በግልጽ ተናግሯል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ወዳጅ በሆነው ቻርሊ ከርክ ላይ የተፈጸመው ግድያ በመላዋ አሜሪካ ድንጋጤን ፈጥሮ እስካሁን ድረስ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

በዩታህ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ለተማሪዎች ንግግር እያደረገ እንዳለ በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው ከርክ በሃይማኖታዊ አቋሙ እና በፖለቲካ ተሳትፎው ከፍተኛ ዝናን ያገኘ ወጣት ነበር።