ቦሪስ ጆንሰን በታደሟቸው ድግሶች ላይ ‘ሰዎች ተቃቅፈው፤ እየጠጡ ያነጉ’ እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች አጋለጡ

ቦሪስ ጆንሰን

የፎቶው ባለመብት, WPA POOL

ታትሟል

ጠቅላይ ሚኒስር ቦሪስ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክልከላን ጥሰው የታደሟቸው ድግሶች ጉዳይ አሁንም በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።

በድግሱ ላይ ተገኝተው የነበሩ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በድግሶቹ ላይ ሰዎች ተቃቅፈው፣ አንዳቸው ሌላኛው ጭን ላይ ተቀምጠው እንደነበርም ተናግረዋል።

በድግሶቹ ማግስት ዶውኒንግ ስትሪት ውስጥ ባዶ የመጠጥ ጠርሙሶች ቆሻሻ መጣያዎችን ሞልተው ነበር።

አንዳንዶቹ ድግሶች እስከ እኩለ ሌሊት አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ ንጋት ቆይተዋል።

ድግሱን ለማስቆም የሞከሩ ሠራተኞች መሳለቂያ ተደርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ በውስጥ አዋቂዎች የወጣውን መረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እንዲሁ በቀላሉ አያልፉትም" ብለዋል።

ሱ ግሬይ የተባሉ ከፍተኛ አመራር ስለእነዚህ ድግሶች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ የኮሮናቫይረስ ክልከላ በተጣለበት ወቅት መርህ ጥሰው ከተከናወኑት ድግሶች ጋር በተያያዘ 126 ቅጣቶች መጣሉ ይታወሳል።

ከቅጣቶቹ አንዱ ቦሪስ ጆንሰን በሰኔ 2020 ከታደሙት የልደት ድግስ ጋር ይገናኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልደት በተጨማሪ ለቀድሞው የሕዝብ ግንኙነታቸው ሊ ቺን በተዘጋጀ የሽኝት ድግስ ላይ በኅዳር 2020 መገኘታቸውን የሚጠቁም መረጃም ተገኝቷል።

ሦስት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ውስጥ አዋቂዎች እንዳሉት፣ ድግሶቹ አካላዊ ርቀት ያልተጠበቀባቸው ነበሩ። የተከናወኑተም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕውቅና ነበር።

የቀድሞው የሕዝብ ግንኙነት ሽኝት ድግስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ብርጭቋቸውን ከፍ አድርገው ይታያሉ።

ፖሊስ ከዚህ ድግስ ጋር በተያያዘ ቅጣት አልጣለባቸውም።

አንድ ውስጥ አዋቂ ድግሱን እንዲህ ገልጸዋል።

"ቢያንስ 30 ሰዎች ነበሩ። ሁሉም ሰው ትከሻ ለትከሻ ገጥሞ ነበር የቆመው። አንድ ሁለት ሰዎች ጭን ላይ የተቀመጡም ነበሩ።"

በልዑል ፊሊፕ ቀብር ዋዜማ፣ ሚያዝያ 2021 የተዘጋጀው ድግስ "ሞቅ ደመቅ ያለ ነበር። ሰዎችም ሲደንሱ ታይተዋል" ተብሏል።

ከድግሱ ይሰማ የነበረው ድምጽ እየጨመረ ሲሄድ የፀጥታ ኃይሎች የድግሱ ታዳሚዎች ወደ ውጪ እንዲወጡ ጠይቀዋቸዋል።

አንድ የዐይን እማኝ እንዳሉት "ድግሱን ወደ ቅጥር ጊቢው አዘዋውሩ ከተባለ በኋላ ሁሉም ሰው መጠጡን እና ምግቡን ይዞ ወጥቷል። ከዚያም መጠጣት ቀጠልን። አንዳንዶች እንዲያውም እዛው ነው ያነጉት"።

ውስጥ አዋቂዎቹ እነዚህ ድግሶች በየሳምንቱ ይካሄዱ እንደነበር ነው የተናገሩት።

"አርብ አርብ ለሚካሄዱን ድግሶች የጥሪ ወረቀት ከሥራ ጽሑፎች ጋር ይደርሰን ነበር።"

ድግሶቹ 'Wine-Time Friday' ወይም የአርብ የወይን መሰናዶ ተብለው ይጠራሉ።

ድግሶቹ አርብ አርብ ቢዘወተሩም በሌሎችም ቀናቶች ይከናወናሉ።

አንድ የቀድሞ ባለሥልጣን "ነምበር 10 ውስጥ የድግስ ትራፊ ቆሻሻ አይታጣም። ባዶ የመጠጥ ጠርሙሶች ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወይም ጠረጴዛ ላይም ይታያሉ" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማርቲን ሬይኖልድስ "የራሳችሁን የመጠጥ ጠርሙስ ይዛችሁ ኑ" የሚል የድግስ ጥሪ ኢሜል መላካቸውም ተሰምቷል።

የዶውኒንግ ስትሪት የፀጥታ ባልደረባ ድግስ ለማስቆም ሲሞክር ተስቆበታል ይላሉ አንድ ውስጥ አዋቂ።

የዩናይትድ ኪንግደም ሕዝቦች የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በሚል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸው ሳለ ከፍተኛ የአገሪቱ አመራሮች በእነዚህ ድግሶች 'ዓለማቸውን መቅጨታቸው' በርካቶችን አስቆጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ግባቸው በሠራተኞቹ መወደድ ይመስላል" ብለዋል አንድ የዐይን እማኝ ።

"ድግሱን አቁሙ አላሉም። አካላዊ ርቀት ጠብቁ አላሉም። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርጉ አላሉም። እንዲያውም እሳቸው የመጠጥ ጠርሙሳቸውን ከፍ እያደረጉ ነበር።"

አንድ ድግስ በመታደም የተቀጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በታደሟቸው ሌሎች ድግሶች ሕግ መጣሳቸውን ክደዋል። በዳውኒንግ ስትሪት በተከናወኑ ድግሶች ሕግ መጣሱንም አላመኑም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ተገኝተው በድግሶቹ ላይ ሕግ አልተጣሰም ብለው ቃል ሲሰጡ የተመለከቱት ውስጥ አዋቂዎች ግን ምስክርነቱ ከእውነታው የራቀ ነው ይላሉ።

"ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ቀጥታ እየተከታተልን ነበር። ሕግ አልተጣሰም ሲሉ በጣም ነው የገረመን። ድግሱ ላይ አብረናቸው ነበርን። ሕግ መጣሱንም ተመልክተናል።"

እነዚህ ድግሶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ሕይወት ላይ ጫና አሳድረዋል።

ሕዝቡ የጣለባቸው እምነት እየተሸረሸረ ነው።

ፓርቲያቸው ሥልጣን እንዲለቅ የሚደረገው ጫናም ቀጥሏል።

በድግሶቹ ሳቢያ በዩኬ የተነሳው ፖለቲካዊ ውዝግብ 'Partygate' በሚል መጠሪያ ይታወቃል።