በኢትዮጵያ፣ በኬንያና ሶማሊያ 14 ሚሊዮን ሕዝብ የረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው ተባለ

ድርቅ

የፎቶው ባለመብት, ERIC LAFFORGUE/ART IN ALL OF US

የምስሉ መግለጫ, በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ድርቅ ካጋጠመባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ይገኙበታል።
ታትሟል

በኢትዮጵያ፣ በኬንያና ሶማሊያ ብቻ 14 ሚሊዮን ሕዝብ የረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው ያሉት በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ድርቅ ርብርብ እንዲደረግ ጠየቁ።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ የተጎጂዎች ቁጥሩ ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአፍሪካ ቀንድ ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ40 በላይ የሚሆኑት እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የከፋ አደጋ ከመከሰቱ በፊት በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙት አገራት ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ 14 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን እና አስፈላጊው ድጋፍ የማይደረግ ከሆነ የተጎጂዎች ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህን ማሳሰቢያ ያወጡት የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በአፍሪካ ቀንድ ስለተከሰተው ድርቅ ነገ ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. ውይይት ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ ነው።

በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት የተጋለጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩት የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በግጭት፣ በአንበጣ መንጋ እና አሁን ደግሞ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በሸቀጦች ዋጋ መናር ምክያት ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብተዋል።

ማሳሰቢያውን ካወጡት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ ክርስቲያን ኤይድ፣ ዳኒሽ ሬፊዩጂ ካውንስል፣ ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል፣ ኦክስፋም፣ ፕላን ኢንተርናሽና እና ዎርልድ ቪዥን ይገኙበታል።

በአፍሪካ ቀንድ ለረሃብ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ከተባሉ 14 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ገሚሱ ሕጻናት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በአካባቢዎቹ የሚጠበቀው ዝናብ ካልጣለ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ጨማሪ አሳይቶ ተጨማሪ ሰዎች ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ ብለዋል።

ዝናብ ቢዘንብ እንኳ ሰዎች ከገቡበት ችግር እስኪያንሰራሩ ድረስ ወራቶች ስለሚወስዱባቸው መንግሥታት እና ድርጅቶች አስቸኳይ ድጋፋ ማድረግ አለባቸው ተብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእአአ 2020 ማብቂያ ላይ የረሃብ አደጋ የተጋረጠባቸው ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ከፍ ሊል ይችላል ሲል ከዚህ ቀደማ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሕይወት አድን ሥራዎችን ለመሥራት 4.4 ሚሊዮን ዶላር የጠየቁ ቢሆንም ከለጋሽ አካላት የተገኘው ገንዘብ ግን እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ተመልክቷል።

ለምሳሌ በሶማሊያ ለሚተገበረው የሰብዓዊ ሥራ ከተጠየቀው መጠን የተገኘው 5 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።