አዳዲስ ማስረጃዎች የሮማን አብራሞቪችን ሕገ-ወጥ ስምምነቶችን አጋለጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮማን አብርሞቪች ሃብት ያፈሩበትን ሕገ-ወጥ ስምምነቶች በተመለከተ ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ አዳዲስ ማስረጃዎች አግኝቷል።
የቼልሲው ባለቤት እአአ በ1995 በተጭበረበረ ጨረታ ከሩሲያ መንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ከገዙ በኋላ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አግኝተዋል።
እአአ በ2005 ሲብኔፍትን ለሩሲያ መንግሥት በ13 ቢሊዮን ዶላር ከመሸጣቸው በፊት አብራሞቪች በ250 ሚሊዮን ዶላር ነበር ድርጅቱን የገዙት።
በወንጀል ድርጊት ብዙ ሃብት አከማችቷል ለሚለው ክስ ምንም ማስረጃ የለም ሲሉ የባለሃብቱ ጠበቆች ይከራከራሉ።
ሩሲያዊው ቢሊየነር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ባለፈው ሳምንት በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
የአብራሞቪች ንብረቶች ሲታገዱ ከቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ዳይሬክተርነታቸውም ተሰርዘዋል።
ሩሲያዊው ቢሊየነር የሲብኔፍትን ስምምነትን ለማግኘት ሕገ-ወጥ ክፍያ መፈጸማቸውን በእንግሊዝ ፍርድ ቤት አምነዋል።
እአአ በ2012 በቀድሞ ሸሪካቸው ቦሪስ ቤርዞቭስኪ ለንደን በሚገኝ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
አብራሞቪች ክሱን ቢረቱም የሲብኔፍትን ጨረታ ለማሸነፍ እንዴት እንደተጭበረበረ እና ቤርዞቭስኪን ለአንድ የክሬምሊን ባለስልጣን ክፍያ እንዲፈጽሙ 10 ሚሊዮን ዶላር እንዴት እንደሰጡ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ፓኖራማ ከሩሲያ በድብቅ ሳይወጣ አይቀርም ተብሎ የሚታመን ሰነድ አግኝቷል።
መረጃው ለቢቢሲ የተሰጠው ስሙ ለደህንነቱ ሲባል በማይገለጽ ምንጭ ነው። የሩሲያ ሕግ አስከባሪ አካላት በአብራሞቪች ዙሪያ ከያዙት ሰነዶች በድብቅ የተቀዳ ነውም ተብሏል።
ቢቢሲ ይህን ማረጋገጥ ባይችልም በሩሲያ ካሉ ሌሎች ምንጮች ጋር ባደረገው ማመሳከር ባለአምስት ገጹ ሰነድ ውስጥ ያሉት ብዙ ጉዳዮች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ሰነዱ እንደሚያስረዳው በሲብኔፍት ስምምነት የሩሲያ መንግሥት 2.7 ቢሊዮን ዶላር የተጭበረበረ ሲሆን ይህ ጥያቄም በ 1997ቱ የሩሲያ ህዝብ እንደራሴዎች ምርመራ የተደገፈ ነው ይላል።
ሰነዱ አክሎም የሩሲያ ባለስልጣናት አብራሞቪችን በማጭበርበር ክስ ሊከፍቱባቸው እንደፈለጉ ይገልጻል።
ፓኖራማ በ1990ዎቹ ስምምነቱን የመረመሩትን የቀድሞውን የሩሲያ ዋና አቃቤ ሕግ ለማግኘት ጥረት አድርጓል።
ዩሪ ስኩራቶቭ ስለ ሚስጥራዊ ሰነድ ባያውቁም ግን ስለ ሲብኔፍት ሽያጭ ብዙ ዝርዝሮችን አረጋግጠዋል።
ስኩራቶቭ ለቢቢሲ ፓኖራማ እንደተናገሩት "በመሰረቱ በፕራይቬታይዜሽኑ ውስጥ የተሳተፉት ሰዎች አብራሞቪች እና ቤርዞቭስኪ መንግሥትን እንዲያታልሉ እና ኩባንያ ያለውን ትክክለኛ ዋጋ እንዳይከፍሉ የሚያደርግ አንድ የወንጀል ቡድን የተቋቋመበት የማጭበርበሪያ ዕቅድ ነበር" ብለዋል።
ሰነዱ አክሎም አብራሞቪች በቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበር ይጠቁማል።
በአብራሞቪች ዙሪያ የተሰበሰቡ ሰነዶች ወደ ክሬምሊን የተዛውሩ ሲሆን በስኩራቶቭ ላይ የተደረገው ምርመራ በፕሬዚዳንቱ መቆሙን ይገልጻል።
ሰነዱ ላይ "ከፕራይቬታይዜሽን ጋር በተያያዘ በተደረገ ምርመራ ስኩራቶቭ ሲብኔፍትን ለመውረስ የሚያስችል የወንጀል ክስ እያዘጋጁ ነበር። ምርመራው በፕሬዝደንት የልሲን እንዲቆም ተደርጓል ... ስኩራቶቭም ከሥራቸው ተባረዋል።"
ስኩራቶቭ ያሉበት የወሲብ ቪዲዮ በ1999 ከተለቀቀ በኋላ ከሥራ ተባረዋል። እሳቸው ግን ምርመራውን ለማጣጣል የተደረገ ድራማ ነው ብለዋል።
"ይህ ሁሉ ነገር በግልጽ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነበር። ምክንያቱም በምርመራዎቼ ከቦሪስ የልሲን ቤተሰብ በጉዳዩ እንዳሉበት ለማረጋገጥ በጣም ተቃርቤ ነበር። ይህ ደግሞ የሲብኔፍት ፕራይቬታይዜሽን ምርመራን ይጨምራል።"
እአአ በ2000 ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ሲመጡም አብራሞቪች በክሬምሊን የቅርብ ሰው ሆነው ቆዩ።
ሰነዱ ከሁለት ዓመት በኋላ ስላቭኔፍት የተባለ የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያን ያካተተ ሌላ የተጭበረበረ ጨረታ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን ይዟል።
አብራሞቪች ስላቭኔፍትን ለመግዛት ከሌላ ኩባንያ ጋር ሽርክና ቢፈጥሩም አንድ የቻይና ኩባንያ እጥፍ የሚጠጋ ዋጋ አቅርቦ ለመጫረት አቅዶ ነበር።
የቻይናው ኩባንያ ጨረታውን ቢያሸንፍ ከክሬምሊን እስከ የህዝብ እንደራሴ ያሉ ብዙ ፈርጣማ ግለሰቦች ይሸነፉ ነበር።
ሰነዱ አክሎም አንድ የቻይና ልዑካን ቡድን አባል ለጨረታ ሞስኮ ሲደርስ ታፍኗል ይላል።
"ሲኤንፒሲ የተባለው የቻይና ኩባንያ በጣም ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረ ሲሆን ከተወካዮቹ መካከል አንዱ ሞስኮ አየር ማረፊያ ሲደርስ ታግቷል። ኩባንያው ከጨረታው መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ነበር ግለሰቡ የተለቀቀው።"
ስለሰነዱ የማያውቁ ገለልተኛ ምንጮች የአፈና ታሪኩ አረጋግጠዋል።
በስላቭኔፍት ሽያጭ ወቅት ቭላድሚር ሚሎቭ የሩሲያ ምክትል የኢነርጂ ሚኒስትር ነበሩ። ስለ አፈና ታሪክ ምንም ዓይነት አስተያየት ባይሰጡም ከጨረታው በፊት ጀምሮ ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች አብራሞቪችና ሸሪካቸው በጨረታው አሸናፊ እንደሚሆን ወስነዋል ብለዋል።
". . . ዋጋው ቀድሞ ስለተወሰነ ስላቭኔፍት ለአብራሞቪች ተሰጠ። ቻይናውያኑ በዚህም በዚያም ተብለው ወጡ።"
አብራሞቪች ስለጠለፋው ሴራ የሚያውቁት ወይም ምንም ዓይነት ሚና እንደተጫወቱ ምንም አልተገለጸም።
ጠበቆቻቸው የአፈና ክሱ "ሙሉ በሙሉ በማስረጃ ያልተደገፈ እና ስለዚህ ክስተት ምንም እንደማያውቁ" ለቢቢሲተናግረዋል።
የተለያዩ ቡድኖች ስላቭኔፍትን ለመቆጣጠር ሲራኮቱ የነበረ ሲሆን በቻይናዊያን ጨረታ ላይም ሰፊ ተቃውሞ ነበር።
ቻይናውያኑ ለቀው የወጡበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን አብራሞቪች የፈጠሩት ሽርክና ጨረታው ላይ የቀረው ብቸኛው ገዢ ነበር። እናም ስላቭኔፍትን በዝቅተኛ ዋጋ ገዙ።
የአብራሞቪች ጠበቆች በስላቭኔፍት እና በሲብኔፍት ስምምነቶች ላይ የተነሱባቸው የሙስና ውንጀላዎች አስተባብለዋል። የየልሲን ጥበቃ ይደረግላቸው ነበር የሚለውንም ክስ ክደዋል።












