የመኪና እሽቅድምድም ኮከቡ ሃሚልተን በእናቱ ስም ሊጠራ ነው

እንግሊዛዊው ሉዊስ ሃሚልተን።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንግሊዛዊው ሉዊስ ሃሚልተን።
ታትሟል

ደረቷ ለመሬት የቀረበች መኪና በፍጥነት በማሸከርከር ይታወቃል። ሰባት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮን ሆኗል።

እንግሊዛዊው ሉዊስ ሃሚልተን።

የ37 ዓመቱ ብሪታኒያዊ የእናቱን ስም በመጠሪያ ስሙ ውስጥ ለማካተት ወስኗል።

ምዕራባዊያን 'ሚድልኔም' የሚሉት ባህል አላቸው። በመጀመሪያ ስማቸው እና በቤተሰብ ስማቸው መካከል የሚገባ። ሃሚልተንም የእናቱ ስም 'ሚድልኔም' እንዲሆንለት ፈልጓል።

"በቤተሰቤ ስም በጣም እኮራለሁ። የእናቴ ስም ላርባሌስቲዬር ነው። ይህን ስም ከመጠሪያዎቼ መሃል እንዲሆን እፈልጋለሁ" ብሏል።

የዚህ ዓመት የመኪና እሽቅድምድም በሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል።

በምዕራባዊያን ባሕል አንዲት ሴት አግብታ ስትወጣ የቤተሰቧንም ስም ጥላ ነው የምትወጣው። ከዚያ በቧላ የቤተሰብ ስም መጠራት ትጀምራለች ማለት ነው።

ሃሚልተን ይህ ለምን ይሆናል ብሏል።

"ሰዎች ሲጋቡ ለምን ሴቷ ስሟን እንደምታጣ እኔ በፍፁም ሊገባኝ አልቻለም" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሜርሴዲስ ለተሰኘው ቡድን የሚወዳደረው ሃሚልተን ስሙን በጋዜጣ ለማስቀየር እየሞከረ ቢሆንም ባህሬይን በሚካሄደው ውድድር ላይ ግን በተለመደው ስሙ እንደሚጠራ አስታውቋል።

የሃሚልተን እናትና አባት የተፋቱት ገና ልጅ ሳለ ነበር።

ዝነኛው አሽከርካሪ ባለፈው ዓመት አወዛጋቢ በሆነ መንገድ የዓለም ቻምፒዮና ሳይሆን በመቅረቱ 'መሪውን ይሰቅላል' የሚል ፍራቻ ነበር።

ሃሚልተን "ተመልሼ የመጣሁት ለስምንተኛ ጊዜ የዓለም ቁንጮ ለመሆን። ለዚያ ነው የመጣሁት" ሲል አስረግጧል።