ወደ ቦሌ ሲጓዙ በነበሩ የቤተሰብ አባላት ላይ በደረሰ አደጋ ተጓዧን ጨምሮ ሰባት ኤርትራውያን ሞቱ

ከሌላ የትራፊክ አደጋ ላይ የተወሰደ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Addis ababa police

የምስሉ መግለጫ, ከሌላ የትራፊክ አደጋ ላይ የተወሰደ ምስል
ታትሟል

ወደ ውጪ አገር የምትሄድ የቤተሰብ አባልን ለመሸኘት በአንድ መኪና ይጓዙ የነበሩ ኤርትራውያን ቤተሰብና ዘመዶቻቸው ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ የተጓዧን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ።

ወደ ውጪ አገር የምትሄደዋን የቤተሰባቸውን አባልና ልጆቿን ለመሸኘት ከገላን ኮንዶሚኒየም ተነስተው እየሄዱ የነበሩ አስራ አንድ ሰዎች የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለቢቢሲ ገልጿል።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ መጋቢት 03/2014 ዓ.ም ምሽት ላይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ከገላን ተነስተው በሃና ማሪያም በኩል ቀለበት መንገዱን ይዘው ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እያቀኑ የነበሩት 11 የአንድ ቤተሰብ አባላትና ዘመዳሞች ነበሩ ተብሏል።

ቤተሰብ ሊሸኛት የተሰበሰበው የውጪ አገር ተጓዥ አብረዋት የሚሄዱ የ4 እና የ6 ዓመት ልጆቿን ይዛ የነበረ ሲሆን፣ ከአሥመራ ድረስ ሊሸኟት የመጡ እናቷ እንዲሁም ሌሎች አዲስ አበባ የሚኖሩ ዘመዶቿ በአንድ ላይ ነበሩ።

አስራ አንድ ሰዎች ተሳፍረው የነበረበት ዶልፊን ሚኒባስ ቦሌ አየር ማረፊያ ለመድረስ መንገዱን ካጋመሰ በኋላ በብልሽት ምክንያት መንገድ ዳር ቆሞ ከነበረ ሲኖትራክ ከባድ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ ለሰባት ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

በአደጋው ከ11ዱ ሰዎች ሰባት ሴቶች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል ወደ ባህር ማዶ የምትሸኘው ተጓዥ፣ ከአሥመራ የመጡት እናቷና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ይገኙበታል።

ከእናታቸው ጋር ወደ ውጪ አገር ሊጓዙ የነበሩት የአራትና የስድስት ዓመቱ ህጻናት ግን ከአደጋው በሕይወት ቢተርፉም ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በሕይወት ከተረፉት ሰዎች መካከል አንዱ የሚኒባሱ አሽከርካሪ ሲሆን ከባድ ጉዳት ደርሶበት ህክምና እየተከታተለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ዘመዳሞች የሆኑት የአደጋው ሰለባዎች ሁሉም ኤርትራውያን ሲሆኑ፣ ከሚኖሩበት ገላን ኮንዶሚኒየም ከሚባለው አካባቢ ተነስተው ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲያቀኑ ነበር እንደወጡ የቀሩት።

አደጋው ከደረሰ በኋላ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው በደረሱበት ወቅት የሰባቱ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ሁለቱን ህጻናትን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችን ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዳቸውን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአደጋው ሰለባዎች በተፈጠረው ከባድ ግጭት ሳብያ በሚኒባሱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ ስለነበር በመኪናው ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈውን ሰዎች አስከሬን ለማውጣት የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ደጋፊ ማሽኖችን ለመጠቀም ተገድደው ነበር።

አቶ ንጋቱ አስከሬኖቹን ክፉኛ ከተጉዳው ዶልፊን ሚኒባስ ውስጥ ለማውጣት እጅግ ፈታኝ እንደነበር አስታውሰው፣ ከአንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ በላይ እንደፈጀባቸው ገልፀዋል።

የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ እንደሚሉት አደጋው የደረሰበት ቦታ በተደጋጋሚ አደጋ የሚከሰትበት መሆኑን እና ከዚህ በፊትም አንድ የፖሊስ አባል ጭምር በዚሁ ስፍራ ሕይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል።

ቦታው ከፍተኛ ቁልቁለት ያለበት ቦታ ሲሆን የፍጥነት መቀነሻ የመንገድ ላይ ማገጃ የሌለው ቦታ መሆኑ ለአደጋዎች መከሰት አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በተከሰተው አደጋ እና በተያያዥ ጉዳዮችን ዙሪያ ፖሊስ ዝርዝር ምርመራ እየተደረገ እና የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑን ቢቢሲ ከፖሊስ ለመረዳት ተችሏል።