አሜሪካዊው ጋዜጠኛ እና የፊልም ባለሙያ ዩክሬን ውስጥ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩክሬን ውስጥ ሲሰራ የነበረ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ ወጣ ብላ በምትገኘው ኢርፒን ከተማ ውስጥ በጥይት ተመቶ መሞቱን ፖሊስ አስታወቀ።
ጋዜጠኛና የፊልም ባለሙያ የነበረው የ50 ዓመቱ ብሬንት ሬናውድ በዩክሬንና በአካባቢዋ ለታይም ሲሰራ ቆይቷል።
የኪዬቭ ፖሊስ ኃላፊ አንድሬ ኔቢይቶቭ እንዳሉት ጋዜጠኛው በሩሲያ ወታደሮች ኢላማ ተደርጎ ነበር። ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችም የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካዊው በጦርነቱ መካከል የተገደለ የመጀመሪያው የውጭ ጋዜጠኛ ሆኗል።
ከቆሰሉት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ሁዋን አሬዶንዶ የተባለው ለአንድ የጣሊያን ጋዜጠኛ እንደተናገረው ከብሬንት ሬናውድ ጋር እንዳሉ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጿል።
"ኢርፒን ውስጥ ከሚገኙ ድልድዮች መካከል ከመጀመሪያው ባሻገር ሆነን ነዋሪዎች ለቀው ሲወጡ በቪዲዮ እየቀረጽን ነበረ" ብሏል።
ከዚያም አንድ ሰው ወደ ሌላ ድልድይ ሊወስዳቸው የፍተሻ ጣቢያውን ካለፉ በኋላ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናግሯል። ብሬንት ሬናውድ በጥይት አንገቱን ተመትቶ ወደ ኋላ መቅረቱንና እሱና ጓደኛው መቁሰላቸውን ገልጿል።
ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ምንም እንኳን ጋዜጠኛው ዩክሬን ውስጥ ለእነሱ እየሰራ የነበረ ባይሆንም በግድያው "በጽኑ ማዘኑን" ባወጠው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ከብሬንት ሬናውድ ለጋዜጠው ለመጨረሻ ጊዜ የሰራው ከሰባት ዓመት በፊት የነበረ ሲሆን ከተገደለ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የነበረው የጋዜጠኛ መታወቂያ ድርጅቱ ከዓመታት በፊት የሰጠው መሆኑን ገልጿል።
ሬናውድ ከዚህ በፊት ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ እና ሄይቲ ውስጥ በጋዜጠኝነት ተሰማርቶ ሰርቷል። በሥራውም አሜሪካ ቺካጎ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ ባቀረበው ሥራ የ'ፒቦዲ አዋርድ' ሽልማትን አግኝቷል።
ሬናውድ ብዙ ጊዜ ሥራውን የሚያከናውነው የፊልም ባለሙያ ከሆነው ከወንድሙ ክሬግ ጋር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ ወንድሙ ወደ ዩክሬን አብሮት ስለመጓዙ የታወቀ ነገር የለም።
ሬናውድ የተሰማው ሌላ ለዩክሬን ቴሌቪዥን የሚሰራው ዩክሬናዊ የካሜራ ባለሙያ ይቬሄኒ ስኩም ኪየቭ ውስጥ የሚገኝ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ማማ በከባድ መሳሪያ ሲመታ ከተገደለ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከሳምንት በፊት ኪዬቭ ውስጥ ለዘገባ የተሰማራ አንድ የብሪታኒያ ጋዜጠኛ በጥይት ተመትቶ ቆስሏል።












