ሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ ከቻይና ጠይቃለች መባሉን አስተባበለች

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ
ታትሟል

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ እያካሄደችው ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ከቻይና ወታደራዊ ድጋፍ ጠይቃለች መባሉን አስተባበለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሩሲያ የጦር መሳሪያ እና የእርዳታ ጥያቄ ለቻይና ማቅረቧን በመግለጽ፣ ቻይና የተጣሉትን ማዕቦች ተላልፋ ለሩሲያ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ "ከባድ መዘዝ" ያስከትላል ሲል የጆ ባይደን አስተዳደር አስጠንቅቆ ነበር።

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለዚሁ የአሜሪካ ባለሥልጣንት ክስ በሰጡት ምላሽ አገራቸው ዩክሬን ውስጥ እያካሄደች ያለውን "ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ ለመቀጠን የራሷ አቅም አላት" ሲሉ ከቻይና ድጋፍ አለመጠየተቃቸውን ገልጸዋል።

ጨምረውም ሩሲያ ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ የምትለው በዩክሬን ላይ ከፈተችው ወረራ በእቅዷ መሰረት እየተከናወነ መሆኑንና "ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

በዩክሬን ላይ ወረራውን ከከፈተች በኋላ ሩሲያ ወታደራዊ እርዳታን ከቻይናን ጠይቃለች ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ባለሥልጣናት ለተለያዩ የአሜሪካ የዜና ማሰራጫዎች መናገራቸው ተዘግቧል።

ሆኖም ይህንን በተመለከተ በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም ብሏል።

ይህ ጉዳይ መሰማቱን ተከትሎ አሜሪካ ለቻይና ማስጠንቀቂያ የሰጠችው ዛሬ ሰኞ በሮም የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገናኝተው ለመምከር ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው።

የዩክሬንና ሩሲያ ግጭት ከተቀሰቀሰ ጊዜ አንስቶ ቤጂንግ የረዥም ጊዜ አጋሯ ለሆነችው ሞስኮ በተጨባጭ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ስለማድረጓ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ ሩሲያ በቅርብ ቀናት ውስጥ በተለይም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከቻይና እንደጠየቀች መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የቻይና መንግሥት ያለው ነገር የለም።

በሌላ ዜና የአውስትራሊያ መንግሥት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተከትሎ በ33 የሩስያ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ነጋዴዎች እና የቅርብ ቤተሰባቸው ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጣል አስታውቋል።

የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ሮማን አብረሞቪች በአውስትራሊያ ማዕቀብ ከሚጣልባቸው ሰዎች አንዱ መሆናቸውም ተሰምቷል።

ይህ በእንዲ እንዳለ ሩሲያና ዩክሬን ለማድረግ ያቀዱት አዲስ ውይይት ከጅምሩ ተስፋ ተጥሎበታል።

የሩስያ ተደራዳሪ እና የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፕሬስ ሴክሬታሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ውይይቱ የሚካሄደው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ነው ብለዋል።

የዩክሬን ተደራዳሪ እና የፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አማካሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ የሩሲያንን መግለጫ አረጋግጠዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ፖዶሊያክ ሩሲያ በውይይቱ ላይ ገንቢ በሆነ መልኩ መሳተፍ ጀምራለች ብሏል።

ሩሲያ አሁን በዙሪያዋ ያለውን ዓለም በተገቢ ሁኔታ ትረዳለች። በጦር ሜዳዎች የዩክሬን ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያላትን ፍላጎት አሳይታለች ሲሉ አክለዋል።

ትላንት ደግሞ ዜሌንስኪ የልዑካን ቡድናቸው ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር በየእለቱ እየተገናኙ እየተነጋገሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሰርቢያ ደግሞ ፑቲንን የሚደግፍ ሰልፍ ታይቷል። በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ በርካታ የሩሲያ መንግሥት ደጋፊዎች ሞስኮ በዩክሬን ላይ ያካሄደችውን ወረራ እንደሚደግፉ ለመግለጽ ነው አደባባይ የወጡት።

ሰልፈኞቹ የሰርቢያን እና የሩሲያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበት በቤልግሬድ ጎዳናዎች ላይ በተደረገው ሰለፍ ለቭላድሚር ፑቲን እና ለሩሲያ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

ይህ ከመሆኑ ከሁለት ቀናት በፊት በከተማው ፀረ-ጦርነት ሰልፍ አቋም የተንጸባረቀበት ሰልፍ ተደርጎ ነበር።