በቤልጂየም መካነ እንስሳት ውስጥ ያሉ ጉማሬዎች በኮቪድ ተያዙ

ጉማሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጉማሬዎቹ እንዴት በቫይረሱ ሊያዙ እንደቻሉ የታወቀ ነገር የለም።
ታትሟል

የቤልጂየም መካነ እንስሳት ሁለት ጉማሬዎቹ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ለይቶ ማቆያ መወሰዳቸውን ገለጸ።

የ14 ዓመቱ ኢማኒ እና የ41 ዓመቷ ሔርሜን እንዴት በቫይረሱ ሊያዙ እንደቻሉ የታወቀ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ በቤልጂየም የሚገኘው አንትወርፕ መካነ እንስሳት እንስሳቱ ከማንዘርዘር [በአፍንጫቸው ፈሳሽ ከመውጣቱ] በስተቀር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ እንስሳቱ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ በመካነ እንስሳቱ ገደቦች እንዲጠበቁ አዟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዱር እና የቤት እንስሳት በሳርስ-ኮቭ 2 መያዛቸውን በርካታ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የጉማሬ አፍንጫ ብዙውን ጊዜ እርጥበት የማያጣው ቢሆንም በአንትዎርፕ መካነ እንስሳት ያሉ ሐኪሞች ሁለቱን ጉማሬዎች እንዲመረመሩ የወሰኑት " በአፍንጫቸው ንፍጥ ሲወጣ" በመመልከታቸው ነበር።

በአሁኑ ወቅት ጉማሬዎቹ አጥር ተዘግቷል፤ ከኮቪድ ነጻ የሆኑ ተቆጣጣሪዎቻቸውም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እና የደህንነት መነጽር ማድረግ ግዴታቸው ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጉማሬዎቹ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ጫማቸውን በጸረ ተህዋስ ፈሳሽ ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል።

በአንትወርፕ መካነ እንስሳት ሐኪም የሆኑት ፍራንሲስ ቨርካሚን " እስከማውቀው ድረስ በዚህ ዝርያ ቫይረሱ ሲተላለፍ የተመዘገበ የመጀመሪያው ክስተት ነው። በዓለም ይህ ቫይረስ በአብዛኛው የታየው በዝንጀሮዎችና በድመቶች ላይ ነው" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ካናዳ ሦስት የዱር አጋዘኖች በኮቪድ-19 መያዛቸውን አስታውቃ ነበር። ይህም በአገሪቷ የዱር እንስሳት የተመዘገበው የመጀመሪያው ሪፖርት ነው።

በእንስሳት ላይ የሚደረገው ምርመራ ውስን በመሆኑ ኮቪድ-19 በዱር ምን ያህል እንደሚስፋፋ አይታወቅም ተብሏል።