ፓንዶራ ሰነዶች፡ የኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰቦች ምስጢራዊ ሀብት ተጋለጠ

ታትሟል

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰቦች አገሪቱ ነጻነቷን ከእንግሊዝ ካገኘችበት ጊዜ አነስቶ በፖለቲካው ዘርፍ በበላይነት ሲመሩ ነበር።

የዓለም መሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና ቢሊየነሮች ምስጢራዊ ሀብትና ስምምነቶች አፈትልከው በወጡበት ሰነዶች የኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰብ በሚስጥር የሚያስተዳድራቸው የተለያዩ ድርጅቶች እንዳሉ ተረጋግጧል።

የፓንዶራ ሰንዶች የሚል ስያሜ የተሰጠውና አፈትልኮ የወጣው ይህ የሰነዶች ስብስብ፤ 12 ሚሊየን ሰነዶች ያሉት ሲሆን በታሪክ ትልቁ አፈትልኮ የወጣ ሰነድ እንደሆነ ተነግሮለታል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ስድስት የቤተሰብ አባላት ከ13 ሚስጥራዊ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ስማቸው ተነስቷል።

እስካሁን በጉዳዩ ላይ የኬንያታ ቤተሰቦች ምንም ያሉት ነገር ያለም።

የኬንያታ ቤተሰቦች ሚስጥራዊ ድርጅቶችና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም እስከ 30 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ አንድ ድርጅት መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ከድርጅቶቹ ጋር በተያያዘም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችና አስተዳደራዊ መረጃዎች ተገኝተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ዕለት የፓንዶራ ሰነዶች ተብለው በተጠሩት ሰነዶች፤ በባሕር ማዶ ኩባንያዎች ሰነዶች ውስጥ 35 የሚሆኑ ሥልጣን ላይ ያሉ እና የቀድሞ መሪዎች እንዲሁም ከ300 በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፋይሎች ይፋ ሆነዋል።

በተገኙት ሰነዶች መሠረት የ88 ዓመት እድሜ ባለጸጋ የሆኑት የኡሁሩ ኬንያታ እናት ንጊና 'ቫሪስ' ተብሎ የተጠራ ፋውንዴሽን የመጀመሪያ ተቆጣጣሪ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ልጃቸው ኡሁሩ ደግሞ እሳቸው ሲሞቱ ወራሽ እንደሚሆኑ በግልጽ ተቀምጧል።

በሰነዶቹ ላይ ግን ተቋሙ ለምን እንደተመሠረተና ምን ያህል ሀብት እንዳለው ምንም የተገለጸ ነገር የለም ተብሏል።

በፓናማ የሚመሠረቱ ፋውንዴሽኖች በበርካቶች የሚፈለጉ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ የተቋሞቹ ባለቤቶችና መስራቾች ከጠበቆቻቸው ውጪ ስማቸውን ማንም እንዲያውቀው ስለማይደረግ ነው። የፓናማ መንግሥትም ቢሆን ስማችሁን ንገሩኝ ብሎ አይጠይቅም።

በዚህ መሠረት የሚመዘገቡት ድርጅቶችና ሀብቶች ያለ ምንም ቀረጥና ሌሎች ክፍያዎች ለወራሽ መተላለፍ ይችላሉ።

በፓንዶራ ሰነዶች የኬንያታ ቤተሰቦች ምን ያህል የተጣራ ሀብት እንዳላቸው ባይገለጽም፤ ቤተሰቡ በትራንስፖርት፣በኢንሹራንስ፣ በሆቴል፣ በግብርና እና በመሬት ባለቤትነት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ኡሁሩ ኬንያታ ከቢቢሲ ሀርድ ቶክ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀብት መጠናቸው በግልጽ እንደሚታወቅና እንደ ፕሬዝዳንትነታቸው ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሀብታቸውን መጠን ማሳወቃቸውን ተናግረው ነበር።

በፓንዶራ ሰነዶች በርካታ ሚስጥሮች ከተጋለጡባቸው የዓለም መሪዎች መካከል የዮርዳኖሱ ንጉሥ ይገኙበታል።

ንጉሥ አብዱላሂ ሁለተኛ ቢን አል-ሁሴን በእንግሊዝ እና በአሜሪካን 70 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ ንብረት በድብቅ ማከማቸታቸው ይፋ ሆኗል።

እአአ በ1999 ሥልጣን ከያዙ ጀምሮም 5 ቤቶችን ለመግዛት በብሪታንያ ቨርጂን ደሴቶች እና ሌሎች የሚገኙ የባሕር ማዶ ኩባንያዎችን ተጠቅመዋል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እና ባለቤታቸውም ቢሆኑ በለንደን ጽሕፈት ቤት ሲገዙ ከቴምብር ቀረጥ 312,000 ፓውንድ እንዴት እንዳተረፉ ያሳያል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሚስታቸው ቼሪ በማዕከላዊ ለንደን የሚገኘውን ሕንጻ በእጃቸው ያስገቡት በሐምሌ 2017 ሲሆን ባለቤት የነበረውን የባሕር ማዶ ኩባንያ በመግዛት ነው።

በዩኬ በተመሳሳይ መንገድ ንብረቶችን ማግኘት ሕጋዊ ሲሆን የቴምብር ቀረጥ መክፈል ላይጠበቅ ይችላል። ሆኖም ብሌር ቀደም ሲል የግብር ክፍተቶችን እያነሱ ተችተዋል።

በፓንዶራ ሰነዶች መሠረት የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሀን የካቢኔ ሚኒስትሮችን እና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚይዙ ኩባንያዎችን በድብቅ ይዘዋል።

በሌላ በኩል በቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ አናስታሲዴስ የተቋቋመው የሕግ ኩባንያ የባለብዙ የባሕር ማዶ ኩባንያዎችን እውነተኛ ባለቤት ለመሸሸግ የሐሰት ባለቤቶችን ያቀረበ ይመስላል። ቀደም ሲል የሩሲያ ፖለቲከኛ የነበሩት ግለሰብም በማጭበርበር ተከሰዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲይሚር ዘለንስኪ የ2019 ምርጫን ከማሸነፋቸው አስቀድሞ ሚስጥራዊ ለሆነ የባሕር ማዶ ኩባንያ ድርሻቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ የምርጫ ፉክክር የሚጠብቃቸው የቼኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬይ ባቢስን፤ በደቡብ ፈረንሳይ ሁለት ቪላዎችን በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ስላገለገለው የውጪ አገር ኢንቨስትመንት ኩባንያ ማሳወቅ አልቻሉም።

ከአስር ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ከሥልጣን እንደሚለቁ ያስታወቁት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በእሳቸውና በቤታሰባቸው ስም ስለተቋቋሙት ፋውንዴሽኖች እና ድርጅቶች የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም።

የኬንያታ ቤተሰብ በርካታ ቁጥር ያላቸው የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማድርግ የጀመረው የኬንያ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት በሆኑት በጆሞ ኬንያታ አማካይነት ነበር።

በርካቶች ጆሞ ኬንያታ ሥልጣናቸውን በመጠቀም በቤተሰባቸው ስም ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት መሰብሰባቸውን ይገልጻሉ።