ፓንዶራ ሰነዶች፡- የዓለም መሪዎች ምስጢራዊ ሐብትና ስምምነቶች ተጋለጡ

ታትሟል

የዓለም መሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና ቢሊየነሮች ምስጢራዊ ሐብትና ስምምነቶች አፈትልከው በወጡ የፋይናንስ ሰነዶች ይፋ ሆኑ።

የፓንዶራ ሰነዶች ተብለው በተጠሩት በባህር ማዶ ኩባንያዎች ፋይሎች 35 የሚሆኑ ስልጣን ላይ ያሉ እና የቀድሞ መሪዎች እንዲሁም ከ300 በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፋይሎች ይፋ ሆነዋል።

የዮርዳኖሱ ንጉስ በእንግሊዝ እና በአሜሪካን 70 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ ንበረት በድብቅ ማከማቸታቸውን ይፋ ሆኗል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር እና ባለቤታቸው በለንደን ጽሕፈት ቤት ሲገዙ ከቴምብር ቀረጥ 312,000 ፓውንድ እንዴት እንዳተረፉ ያሳያል።

ባልና ሚስቱ የሕንፃውን ባለቤት የሆነ የውጭ ሃገር ኩባንያ ገዝተዋል።

የተለቀቀው ፋይል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ሞናኮ ከሚገኙ ምስጢራዊ ንብረቶች ጋር ያገናኛቸዋል።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ የምርጫ ፉክክር የሚጠብቃቸው የቼኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬይ ባቢስን፤ በደቡብ ፈረንሳይ ሁለት ቪላዎችን በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ስላገለገለው የውጪ ሃገር ኢንቨስትመንት ኩባንያ ማሳወቅ አልቻሉም።

የአሁኖቹ ሰነዶች ከፊንሴን ፋይሎ፣ ከፓራዳይዝ ፋይሎች፣ ከፓናማ ፋይሎች እና ለሉክስሊክስን በመከተል በባለፉት ሰባት ዓመታት ይፋ የተደረገ የቅርብ ጊዜ መረጃ ነው።

የፋይሎቹ ምርመራ በዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ማህበር (አይሲአይጄ) የተደራጀ ትልቁ ሲሆን ከ650 በላይ ዘጋቢዎች ተሳትፈውበታል።

ቢቢሲ ፓኖራማ ከጋርዲያን እና ከሌሎች የሚዲያ አጋሮች ጋር በጋራ ባደረገው ምርመራ በብሪታንያ ቨርጂን ደሴቶች፣ ፓናማ፣ ቤሊዝ፣ ቆጵሮስ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሲንጋፖር እና በስዊዘሪላንድ በ 14 የፋይናንስ አገልግሎት ኩባንያዎች ፋይሎች እና ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰነዶችን አግኝተዋል።

አንዳንዶች በሙስና፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና በዓለም አቀፍ ግብር የመሰወር ክሶች ተከፍተውባቸዋል።

ይፋ ከተደረጉት ታላላቅ ጉዳዮች አንዱ ታዋቂ እና ሐብታም ሰዎች በዩኬ ውስጥ ንብረት በድብቅ ለመግዛት ኩባንያዎችን በሕጋዊ መንገድ ማቋቋማቸው ነው።

ሰነዶቹ ከግዢዎቹ በስተጀርባ ስለሚገኙ 95,000 የባህር ማዶ ኩባንያዎችን ባለቤቶችን ማንነነት ይገልጣሉ።

ይህም የእንግሊዝ መንግሥት በተደጋጋሚ የባሕር ማዶ ባለቤቶችን ያለመመዝገብ ስሀተቱን ያሳያል። አንዳንድ የንብረት ገዢዎች ገንዘብ የማጭበርበር ድርጊቶችን ሊደብቁ ይችላሉ በሚል ስጋት ምዘገባ እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ቃል ተገብቶ ነበር።

የገዛ ሀገራቸውን ይዘርፋሉ ተብለው የተከሰሱት የአዘርባጃኑ ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ እና ቤተሰቦቻቸው ለዚህ አንድ ምሳሌ ናቸው።

ምርመራው አሊዬቭ እና የቅርብ ወዳጆቻቸው እንግሊዝ ውስጥ በድብቅ ከ 400 ሚሊዮን ፓውንድ በሚበልጥ የንብረት ግዢ ውስጥ ተሳትፈዋል።

በሰነዶቹ ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ግብይቶች ሕገወጥነት አልተፈጸመባቸውም።

የአይሲአይጂው ባልደረባ ፈርጉስ ሺየል "በዚህ ልክ ምንም ነገር አልነበረም። የባህር ማዶ ኩባንያዎች ሰዎች ብዙ ገንዘብ እንዲደብቁ ወይም ግብርን እንዲሰውሩ ስለማገዛቸው እውነታውን ያሳያል" ብለዋል።

አክለውም "እነዚያ የባህር ማዶ አካውንቶችንተጠቅመው በሌሎች ሃገሮች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚገመት ንብረት ለመግዛት እና በዜጎቻቸው ወጪ የራሳቸውን ቤተሰቦች ለማበልጸግ እየተጠቀሙ ነው" ብለዋል።

አይሲአይጂ ምርመራው ለብዙ ነገሮች ዓይንን ይከፍታል ብሎ ያምናል። ስለሆነም የፓንዶራ ሰነዶች የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

የዮርዳኖስ ማሊቡ መኖሪያ ቤቶች

ሰነዶቹ የዮርዳኖሱ ንጉስ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ከ 100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ የንብረት እንዴት በድብቅ እንደሰበሰበ ያሳያል።

እአአ በ 1999 ስልጣን ከያዙ ጀምሮ አብዱላሂ ሁለተኛ ቢን አል-ሁሴን 15 ቤቶችን ለመግዛት በብሪታንያ ቨርጂን ደሴቶች እና ሌሎች የሚገኙ የባህር ማዶ ኩባንያዎችን ተጠቅመዋል።

ቶኒ እና ቼሪ ብሌር ሐብታቸውን ስለመደበቃቸው በፓንዶራ ሰነዶች ውስጥ ምንም የተባለ ነገር የለም።

ባልና ሚስቱ 6.45 ሚሊዮን የሚያወጣ ንብረት ሲገዙ የቴምብር ቀረጥ ለምን ስላለመክፈላቸው ሰነዶች ያሳያሉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሚስታቸው ቼሪ በማዕከላዊ ሎንዶን የሚገኘውን ሕንጻ በእጃቸው ያስገቡት በሐምሌ 2017 ሲሆን ባለቤት ነበረውን የባህር ማዶ ኩባንያ በመግዛት ነው።

በዩኬ በተመሳሳይ መንገድ ንብረቶችን ማግኘት ሕጋዊ ሲሆን እና የቴምብር ቀረጥ መከፈል ላይጠበቅ ይችላሰል። ሆኖም ብሌር ቀደም ሲል የግብር ክፍተቶችን እያነሱ ተችተዋል።

ሌሎች ሰነዶች ደግሞ የአዘርባጃን ገዥ አሊዬቭ ቤተሰብ የባህር ማዶ ኩባንያዎችን በመጠቀም ንብረት በድብቅ እንግሊዝ ውስጥ እንዴት እንዳገኙ ያሳያሉ።

ፋይሎቹ በአውሮፓ ለረጅም ጊዜ በሙስና የሚከሰሱት ቤተሰቦች ለንደንን ውስጥ ለ11 ዓመቱ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ሄይደር አሊዬቭ የተገዛውን የ 33 ሚሊዮን ፓውንድ ቢሮ ጨምሮ 17 ንብረቶችን እንዴት እንደገዙ ያሳያል።

በሜይፈር ውስጥ ያለው ሕንጻ እአአ በ 2009 የፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ የቤተሰብ ጓደኛ በሆነ ኩባንያ ተገዝቷል።

ከአንድ ወር በኋላ ወደ ሄይድር ስም ተዛወረ።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በጠንካራ ህጎች እና አፈጻጸም በሕገ -ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል። የፓርላማው ጊዜ በሚፈቅድበት ወቅት የእንግሊዝ ንብረት የያዙ የባህር ማዶ ኩባንያዎችን ምዝገባ እንደሚያስተዋውቅ ገልጿል።

በፓንዶራ ሰነዶች ከተጋለጡ ሌሎች ጉዳዮች መካከል-

  • የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ስድስት የቤተሰባቸው አባላት የባህር ማዶ ኩባንያዎችን በድብቅ ይዘዋል። ነስማቸው ከ 11 ድርጅቶች ጋር የተያያዘ ሲሆን አንደኛው ብቻ 30 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገምቷል።
  • የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን አባላት፣ የካቢኔ ሚኒስትሮችን እና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚይዙ ኩባንያዎችን በድብቅ ይዘዋል።
  • በቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ አናስታሲዴስ የተቋቋመው የሕግ ኩባንያ የባለብዙ የባህር ማዶ ኩባንያዎችን እውነተኛ ባለቤት ለመሸሸግ የሐሰት ባለቤቶችን ያቀረበ ይመስላል። ቀደም ሲል የሩሲያ ፖለቲከኛ የነበሩት ግለሰብ በማጭበርበር ተከሰዋል። ሆኖም የሕግ ባለሙያው ይህንን ያስተባብላሉ።
  • የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲይሚር ዘለንስኪ የ 2019 ምርጫን ከማሸነፋቸው አስቀድሞ ሚስጥራዊ ለሆነ የባህር ማዶ ኩባንያ ድርሻቸውን አስተላልፈዋል።