ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሁለት ሰዎች ግድያ ስትፈለግ የነበረችው ኬንያዊት ፖሊስ ሞታ ተገኘች
ሁለት ሰዎችን በጥይት ገድላለች በሚል ስትፈለግ የነበረችው ኬንያዊት ፖሊስ ሞታ እንደተገኘች ተገልጿል።
ግለሰቧ በቤተሰቦቿ ቤት ውስጥ ነው ሞታ የተገኘችው።
ጆርጅ ናቴምቤያ የተባለ የክልል አስተዳዳሪ እንዳሉት ካሮሊን ካንጎጎ የተባለችው ፖሊስ ቤተሰቦቿ ቤት ሄዳ ራሷን በጥይት ገድላለች ብለዋል።
የቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤትም እልጌዮ ማራክዌት ግዛት ሲሆን በስምጥ ሸለቆውም አካባቢ ነው የሚገኘው።
ለሳምንታት ያህል የደህንነት ቡድኖች ተጣምረው ሲፈልጓትም ነበር። ግለሰቧን "የታጠቀችና አልሞ ተኳሽም" ናት በማለት ሲያስጠነቅቅ ነበር።
በናኩሩ እና ኪምቡ አካባቢዎች በሁለት ቀናት ልዩነት ሁለት ወንዶችን ገድላለችም ተብሏል።
አንደኛው ሟች የስራ ባልደረባዋ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ተነግሯል።
ስትታደን የነበረችው ፖሊስ አስከሬንም በአገሪቱ ምዕራብ በኩል በእልጌዮ ማራካዌት ግዛት የተገኘው በዛሬው ዕለት አርብ ነው።
ወላጆቿ ከአንድ ሳምንት በፊት በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው እጇን ለፖሊስ እንድትሰጥ ሲማፀኗት ነበር።
ካሮሊን ካንጎጎ ከዚህ ቀደም በናኩሩ ፖሊስ ጣቢያ በወንጀል ቢሮ ትሰራ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በፍርድ ቤቶች ተዛውራ ስትሰራ ነበር ተብሏል።
ካሮሊን በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠነች እና ልምድ ያላት መኮንን እንደሆነች ተገልጿል።