ዴንማርክ 35ሺህ ሕዝብ የሚያኖረው ሰው ሰራሽ ደሴት ልትገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, DANISH GOVERNMENT
የዴንማርክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮፐንሃገን ወደብን ለመጠበቅ 35ሺህ ሕዝብ ማኖር የሚችል ሰው ሰራሽ ደሴት እንዲገነባ ወሰነ።
ይህ ግዙፍ ሰው ሰራሽ ደሴት ከሌሎች የመሬት ዳርቻዎች ጋር በቀለበት መንገድ እና በሰው ሰራ ዋሻ ይገናኛል ተብሏል።
1 ስኬወር ማይል የሚሰፋው የደሴት ግንባታ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ግንባታው ይጀመራል። ግንባታው በርካታ ዓመታትን እንደሚፈጅ ተገልጿል። መሠረቱ እአአ 2035 የሚጠናቀቅ ሲሆን ደሴቱ ተገንብቶ የሚጠናቀቀው ደግሞ 2070 እንደሆነ ተጠቁሟል።
የዚህ ደሴት ግንባታ እቅድ ግን ከአካባቢ መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ ተቃውሞን አስነስቷል። የደሴቱን ግንባታ የተቃወሙ የአከባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።
ለግንባታው የሚያስፈልጉ ቁሶችን ወደ ግንባታ ስፍራ ለመውሰድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሸርከርካሪ የሚያመነጨው ብክለት አንዱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።
የአከባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት እስከ 350 የሚሆኑ ግዙፍ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች መዲናዋን አቋርጠው ወደ ግንባታው ስፍራ ሊያመሩ ይችላሉ ይላሉ።
400 የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክለውን ደሴት ለመገንባታ 80 ሚሊዮን ቶን አፈር ወደ ግንባታው ስፍራው ማንቀሳቀስን ይጠይቃል።
ከዚህ በተጨማሪም የደሴቱ ግንባታ በአከባቢው የተፈጥሮ ውሃ ሃብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል በማለት ይከራከራሉ።
ፓርላማው የግንባታውን እቅድ ማጽደቁን ተከትሎ ግንባታውን የተቃወሙ ሰልፈኞች ፓርላማው ፊት ለፊት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከተቃዋሚዎቹ አንዷ የሆነችው ኤቫ ላርሰን፤ "ግዙፍ የጭነት መኪኖች መዲናዋን በየዕለቱ እንደሚያቋርጡ ሳስብ ከፍተኛ ስጋት ይገባኛል" ትላለች።
ኒኮላስ ውልሄድ የተባለ ሌላ ተቃዋሚ ደግሞ፤ ይህ በዴንማርክ ታሪክ ትልቁ ነው ያለው ፕሮጄክተር ፍቃድ ሲሰጠው የሕዝቡ ፍላጎት ምን እንደሆነ አልታየም ብሏል።
የዴንማርክ ባለስልጣናት ግን የደሴቱን ግንባታ ሂደት በአካባቢ የአየር ሁኔታ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል ይላሉ።
የግንባታ ቁስ የሚያጓጉዙት የጭነት መኪኖች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።












