ማንችስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሪምየር አሸናፊ ሆነ

የማንችስተር ሲቲ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ማንችስተር ሲቲ በአራት ዓመታት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆኗል።

ትናንት ምሽት በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በሌስተር ሲቲ መሸነፉን ተከትሎ ነው ሲቲዎች አሸናፊነታቸውን ያረጋገጡት።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን አሸናፊነቱን ያረጋገጠው ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩ ከማንችስር ዩናትድ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት10 በመሆኑ ነው።

ማንችስተር ሲቲ የዘንድሮውን ጨምሮ በአጠቃላይ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሰባት ጊዜ አሸናፊ መሆን ችለዋል። ይህ ደግሞ በዘጠኝ ዓመት ውስጥ አምስተኛ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫቸው ነው።

''በጣም አስገራሚና ከሌሎች ጊዜዎች በጣም የተለየ ድል ነው'' ብሏል ጋርዲዮላ።

''የዘንድሮው በጣም ከባድ ነበር። መቼም ቢሆን የዘንድሮውን ድላችንን እናስታውሰዋለን። የዚህ ቡድን እና የነዚህ ተጫዋቾች አሰልጣኝ በመሆኔ በጣም ኩራት ይሰማኛል። . . . 'ከዚህ በፊት ስፔን አሰልጥኛለሁ፣ ጀርመንም አሰልጥኛለሁ፤ ነገር ግን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በጣም ከባዱ ነው'' ብሏል ጋርዲዮላ።

50ኛ ዓመቱን የደፈነው ፔፕ ጋርዲዮላ በአውሮፓውያኑ 2016 የጀርመኑን ባየርን ሙኒክ ለቆ ነበር ወደ እንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ የመጣው። በእነዚህ ስምንት ዓመታት ደግሞ 8 ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።

ሲቲዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ የነበራቸውን ጨዋታ አሸንፈው ቢሆን ቀደም ብለው ዋንጫውን ማንሳተቸውን ማረጋገጥ ይችሉ የነበረ ቢሆንም በቼልሲ ሁለት ለአንድ ተሸንፈዋል።

ማንችስተር ሲቲዎች ከሳምንታት በፊት በካራባዎ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ቶተንሀምን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት የቻሉ ሲሆን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ከቼልሲ ጋር ይገናኛሉ።

ሲቲዎች በሚቀጥለው ሳምንት ከኤቨርተን ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ የሚያነሱ ሲሆን በአዲሱ መመሪያ መሰረት ደግሞ እስከ 10 ሺ የሚደርሱ ደጋፊዎች ገብተው ጨዋታውንና ስነ-ስርአቱን መከታተል ይችላሉ።

የማንችስተር ሲቲ አምበል ብራዚላዊው ፈርናንዲንሆነ ቡድኑን መምራት 'ትልቅ ክብር' እንደነበር ገልጿል።

''ይህን ዋንጫ በማንሳታችን በጣም ኮርቻለሁ፤ በጣም ተደስቻለሁ። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከዓለማችን በጣም ከባዱ ሊግ ነው። እያንዳንዱ ጨዋታ በጣም ከባድ ነው። ዋንጫውን ማንሳታችን ለእኔም ሆነ ለመላው ቡድኑ ትልቅ ስኬት ነው'' ብሏል።

ሲቲን በቅርብ ርቀት ሲከታተል የነበረው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኙ ሶልሻየር በበኩሉ "የውድድር ዓመቱ ሊጠናቀቅ 10 እና 12 ቀናት እስከሚቀሩት ድረስ ተፎክረናል። ማንችስተር ሲቲ በጣም ምርጥ ቡድን ነበር'' ብሏል።