ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ቻይና ''የውሸትና የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል'' በማለት ሁለት የሕዝብ እንደራሴዎችን ጨምሮ ዘጠኝ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
የዩኬ መንግሥት ሰኞ ዕለት በቻይና የኡጉር ሙስሊሞች ላይ ይፈጸማሉ ባላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ነው ቻይና ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈችው።
ሰር ሌይን ደንከን ስሚዝ በቻይና ኢላማ ውስጥ ከገቡት ሰዎች መካከል ሲሆኑ ሌሎች ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸውም ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።
እንደራሴው በቻይና የተጣለባቸውን ማዕቀብ እንደ ክብር ኒሻን እንደሚቆጥሩት ገልጸዋል።
ምንም እንኳን የቅርቡ ማዕቀብ በዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ላይ ቢሆንም ከዚህ በፊትም የአውሮፓ ሕብረትም ማዕቀብ ተጥሎበት ነበር። የአውሮፓ ሕብረት ከዩኬ መንግሥት፣ አሜሪካ እና ካናዳ ጋር በመሆን ሰኞ ዕለት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር።
ቻይና የኡጉር ሙስሊም ዜጎቿን በሺንጂያንግ ግዛት ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል አካባቢ በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የምታቆያቸው ሲሆን በርካቶችም ድብደባ፣ የጉልበት ሥራና ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
ቻይና በበኩሏ የሚቀርቡትን ክሶች በሙሉ እንደማትቀበለው ያስታወቀች ሲሆን፤ ማዕከላቱም ቢሆኑ ሽብርን ለመከላከል ዜጎችን ማሰልጠኛና ማስተማሪያ ናቸው ስትል ትከራከራለች።
በቻይና ማዕቀብ የተጣለባቸው ዘጠኙ ዜጎች የሕዝብ እንደራሴዎቹ ሰር ሌይን፣ ቶም ቱገንዳት፣ ኒይል ኦብራያን፣ ቲም ሎውተን እና ኑስራት ጋኒ ሲሆኑ፤ የሥራ ባልደረቦቻቸው ሎርድ አልተን እና ባሮነስ እንዲሁም የሕግ ባለሙያው ሰር ጎድፍሪ ኒስ እና ምሁሩ ጆ ስሚዝ ፊንሊ ይገኙበታል።
እኚህ ዘጠኝ ዜጎች ወደ ቻይና፣ ሆንግ ኮንግ እና ማካው እንዳይገቡ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን በቻይና የሚገኙ ንብረቶቻቸው በሙሉ በማንኛውም መንገድ እንዳይነቀሳቀሱ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም የቻይና ዜጎችና ተቋማት ከነዚህ ግለሰቦች ጋር ምንም አይነት ሥራ መስራት አይችሉም።
የቀድሞው ወግ አጥባቂ እንደራሴ ሰር ሌይን ''የቻይና መንግሥት እየፈጸማቸው ባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የምናደርገው እንቅስቃሴ ከኃላፊነት ስሜት የመነጨ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።
''እኛ በሕግ የበላይነት ስር በነጻነት ሕይወታችንን የምንመራ ሰዎች ድምጻቸው ለታፈደኑ ሰዎች ድምጽ ልንሆናቸውና መብታቸቀውን ልናስጠብቅላቸው ይገባል። ይህ ተግባር የቻይና መንግሥትን የሚያስቆጣና ማዕቀብ የሚያስጥል ከሆነ ግን ማዕቀቡን እንደ ኒሻን ሽልማት ነው የምቆጥረው'' ብለዋል።
ሌላኛው ማዕቀብ የተጣለባቸው ሚስ ስሚዝ ፊንሌይ በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስፈሩት መልዕክት ''እየተፈጸመ ስላለው ነገር በመናገሬ ምንም ቁጭት አይሰማኝም። ከዚህ በኋላም ቢሆን መናገሬን እቀጥላለሁ'' ብለዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደግሞ ዩኬ ቻይና ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያስተላለፈቸው ውሳኔ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስና መሠረታዊ የሆኑ አሰራሮችን የሚጣረስ እንደሆነ ገልጸዋል።
''ይህ ውሳኔ በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ነው። ለዚህንም በቻይና እና በዩኬ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ይጎዳዋል'' ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገሩ የሚገኙትን የእንግሊዝ አምባሳደር ጠርተው በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸውንና ውሳኔውን በእጅጉ እንደሚቃወሙት መግለጻቸውን አስታውቀዋል።