ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዋይት ሃውስ ማይክሮሶፍት ላይ ያነጣጠረ የኢሜል ጥቃት 'ስጋት' እንዳለ አስጠነቀቀ
አሜሪካ በማይክሮሶፍት ኤክስጄንች ኢሜል ሶፍትዌሮች ላይ የብርበራ ስጋት መኖሩን አሳሰበች።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ከዚህ ቀደም ከቻይና የኢሜይል ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ሲል ነበር።
የዋይት ሃውስ የፕሬስ ፀሀፊ ጄን ፕሳኪ አርብ ዕለት "ይህ በየትኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ጥቃት ነው። እነዚህን ሰርቨሮች የሚያስተዳድሩ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና የትምህርት ተቋማት እርምጃ መውሰድ አለባቸው" ብለዋል።
ማይክሮሶፍት መረጃ ሰርሳሪዎች ጥቃት ለማድረስ የሜይል ሰርቨርን ተጠቅሟል ይላል። ይህን የሜይል ሰርቨር የሚጠቀሙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ድርጅቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተዘግቧል።
አሜሪካ የቻይናን መንግሥት በሳይበር ስለላ ስትከስ ብትቆይም ቤጂንግ ግን ታስተባብላለች።
ፕሳኪ ዋይት ሃውስ ለተገኙ ጋዜጠኞች የማይክሮሶፍት ሰርቨር "በርካታ ተጠቂዎች መኖራቸው እንዳሳሰባቸው" ገልጸው፤ በማይክሮሶፍት ሰርቨር ውስጥ የተፈጠረው ተጋላጭነት "ከፍተኛ ተጽዕኖዎች ሊኖረው ይችላል" ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት "ተጋላጭ የሆኑ ድርጅቶች አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰዳቸው አስፈላጊ ነው" ብሏል፡፡
ስለጥቃቱ ምን እናውቃለን?
የማይክሮሶፍት ሥራ አስፈፃሚ ቶም በርት ሰርሳሪዎች የማይክሮሶፍት ሰርቨሮች እንዲያጠቁ አስችሏቸዋል ያሏቸውን የደህንነት ጉድለቶችን ለመሸፈን የሚያስችሉ ለውጦች መደረጋቸውን ይፋ አደርገዋል።
የማይክሮሶፍት ትሪት ኢንተለጀንስ ሴንተር (ኤም ኤስ ሲ ሲ) ጥቃቱን ያደረሰው ቡድን እራሱን ሃፍኒየም ብሎ የሚጠራ፤ መቀመጫውን በቻይና ያደረገ እና በቻይና መንግሥት የሚደገፍ ነው ብሏል።
ማይክሮሶፍት እንደሚለው ከሆነ ይህ መረጃ በርባሪ ቡድን የተላላፊ በሽታ ተመራማሪዎች፣ የሕግ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከመከላከያ ጋር የሚሠሩ ቡድኖችን መረጃ ለመስረቅ ሞክሯል።
የቻይና መንግሥት ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሃገሪቱ ከብርበራው ጀርባ አለመሆኗን ተናግረዋል።
በአሜሪካ ከ20 ሺህ በላይ ድርጅቶች የተጠቁ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ብዙ ተጎጂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ የሳይበር ደህንነት እና የመሠረተ ልማት ደህንነት ድርጅቶች እራሳቸውን ከመሰል ጥቃት ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስቸኳይ መመሪያን ይፋ አደረጓል።
የዋይት ሃውስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን ድርጅቶች የበይነ መረብ የደህንነት መጠበቂያዎቹን በተቻለ ፍጥነት እንዲያወርዱ አሳስበዋል።
ማይክሮሶፍት የተጠቀሰውን አሃዝ ባያረጋግጥም አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከአሜሪካ የመንግሥት ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።