ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖፕ ፍራንሲስ በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር የነበሩ የኢራቅ ግዛቶች እየጎበኙ ነው
ፖፕ ፍራንሲስ በኢራቅ እያደረጉ በሚገኙት ታሪካዊ ጉዞ በሦስተኛው ቀን ውሏቸው በጽንፈኛው ቡድን አይ ኤስ ተይዘው ቆዩትን የሰሜን ኢራቅን አካባቢዎች እየጎበኙ ነው።
ታጣቂዎች በጎርጎሮሳዊያኑ 2014 አከባቢውን ተቆጣጥረው ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን አፍርሰዋል፤ ዘርፈዋል።
አይ ኤስ በ2017 ተሸንፎ ስፍራውን ከለቀቀ በኋላ ክርስቲያኖች ወደዚያ እየተመለሱ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ኤርቢል ከተማ በሚገኝ ስታዲየም እስከ 10,000 የሚደርሱ ታዳሚዎች በተገኙበት ጸሎት አድርገዋል።
ሥነ ሥርዓቱ ለኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ኢራቅ ባለፈው ወር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ እና ጉብኝቱ ካስከትላቸው የፀጥታ ስጋቶች ጋር ተደምሮ ጉብኝቱ እስካሁን ከተደረጉት አደገኛው ነው ተብሏል።
የ84 ዓመቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ እና አብረዋቸው ያሉት ሁሉ ክትባት ቢወስዱም ኢራቅ ግን የመጀመሪያውን ክትባት የተረከበችው ባለፈው ሳምንት ነበር።
አንዳንድ የሺአ ታጣቂ ቡድኖች የፖፕ ፍራንሲስ ጉብኝትን ምዕራባውያን በሃገሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትን ያሳያል በሚል ተቃውመውታል።
ጳጳሱ እሑድ ለዓመታት በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር የነበረው ሞሱልን የሚጎበኙ ሲሆን በቤተ-ክርስቲያን ተገኝተው በጦርነቱ ህይወታቸው ላለፉት በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ፀሎት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመቀጠልም በአይ ኤስ በከፊል የፈረሰውን ትልቁን የኢራቅ ቤተክርስቲያን ይጎበኛሉ።
ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ የኢራቅ የፀጥታ ኃይሎች ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰማሩ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠርም ሰዓት እላፊዎች ታውጀዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ ምን መልእክት እያስተላለፉ ነው?
ፖፕ ፍራንሲስ አርብ ባግዳድ ከደረሱ ጀምሮ ሁከትና አክራሪነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። በኢራቅ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣው ክርስቲያኖች ሙሉ መብት እና ነፃነት ጎልቶ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ቅዳሜ ከታላቁ አያቶላህ አሊ አል-ሲስታኒ ጋር ናጃፍ ውስጥ ባደረጉት ውይይት ክርስቲያኖች እንደሌሎች ኢራቃውያን ሁሉ በሰላም እና በደህንነት መኖር መቻል አለባቸው ብለዋል።
የሁለቱ ውይይት ለ50 ደቂቃዎች ያህል የቆየ ሲሆን ሁለቱም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ ሲነጋገሩ ነበር።
በመቀጠለም ፖፕ ፍራንሲስ የአብርሃም የትውልድ ቦታ ነው ተብሎ የሚትታመነውን ጥንታዊቷን የዑር ከተማን ጎብኝተዋል።
በዑር ባስተላለፉት መልዕክት "ሽብርተኝነት ሃይማኖትን ሲበደል እኛ አማኞች ዝም ማለት አንችልም ... የሰማይ ብርሃን በጥላቻ ደመና እንዲሸፈን አንፍቀድ" ብለዋል።
የኢራቅ ክርስቲያኖች ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው?
በዓለማችን ካሉ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የክርስቲያን ማህበረሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት የኢራቅ ክርስቲያኖች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ቁጥራቸው ከ 1.4 ሚሊዮን ወደ 250,000 ዝቅ ብሏል።
ይህም ከአጠቃላዩ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከአንድ በመቶ በታች ያደርጋቸዋል።
በጎርጎሮሳወያኑ 2003 አሜሪካ መራሹ ጦር ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ካወረደ ወዲህ በሃገሪቱ የተከሰተውን ብጥብጥ ለማምለጥ ብዙዎች ተሰደዋል።