ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለጨረታ የቀረበው የጃክ ዶርሲ የመጀመሪያው ትዊት በ2.5 ሚሊዮን ዶላር ገዢ አገኘ
የትዊተር መስራች ከሆኑት መካከል አንዱ ጃክ ዶርሲ በትዊተር ገጹ ላይ የለጠፋቸውን የመጀመሪያ ትዊቶች በጨረታ ለሽያጭ አቅርቦ የመጀመሪያው ትዊት ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር መሻገሩ ተነገረ።
በ2.5 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ጥያቄ የቀረበበት ትዊት፤ የጨረታው አሸናፊ ትዊቱን ስለመግዛቱ ዲጂታል ሰርተፊኬት ይቀበላል ተብሏል።
ጃክ ዶርሲ እአአ 2006 ላይ "Just setting up my twttr," ነበር ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ትዊተር ላይ የጻፈው።
የጃክ የመጀመሪያ ትዊት ብትሸጥም በትዊተር ላይ ትቆያለች።
አሸናፊው ተጫራች የሚቀበለው ዲጂታል ሰርተፊኬት በጃክ ዶርሲ የተረጋገጠ እና የተፈረመ ይሆናል። ዲጂታል ሰርተፊኬቱ የመጀመሪያ ትዊት መቼ ትዊት እንደተደረገች፣ የትዊቱ ይዘት እና መሰል መረጃዎችን የያዘ ይሆናል።
ይሁን እንጂ በዲጂታል ሰርተፊኬቱ ላይ የሰፈቱት መረጃዎች ማንኛውም የትዊተር ተጠቃሚ በትዊተር ላይ ሊመለከተው የሚችል ነው።
ጨረታው የወጣው 'ቫሊዩብል ባይ ሴንት' በሚሰኝ ድረ-ገጽ ላይ ሲሆን፤ የደረ-ገጹ መሥራቾች ሰዎች ገንዘባቸውን ወጪ አድርገው መሰል ዲጂታል ሰርተፊኬቶችን ቢይዙ አዋጭ የሆነ ኢንቨስትመንት ነው ይላሉ።
የቢቢሲ የቴክኖሎጂ ዘጋቢ ሮሪ ኬለን-ጆነስ ትዊቶችን በብሎክቼይን አማካኝነት ዲጂታል ገንዘብ እየሆኑ መጥተዋል ይላል።
ለአብዛኞቻችን አንድን ትዊት 2.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጎ መግዛት የማይታሰብ ሊሆን ይችላል ይሁን እንጂ ይህን የመጀመሪያ ትዊት ከትዊተር መሥራች ከሆነው ዶርሲ ጋር አንዳች ቁርኝነት እንዳለው በማሰብ ዋጋ ይሰጡታል።
ሮሪ ምናልባት ሌላ ገዢ ወደፊት ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጎ የመግዛት ፍላጎት ሊኖረው ይችላል ሲል ይናገራል።