ኮሮናቫይረስ፡ የዕድሜ ባለጠጋዎቹ ጥንዶች በእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ተሞሸሩ

ፒተርና ጂን
ታትሟል

በዊልቲሸር በሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ የሚኖሩ የ85 ዓመት አዛውንት 91 ዓመት የሞላቸውን ፍቅረኛቸውን በማዕከል ውስጥ አግብተዋል።

ይህ የዕድሜ ባለፀጋዎቹ ጋብቻ ሊፈፀም የቻለው የአካባቢው አስተዳደር በሰጠው ልዩ ፍቃድ መሆኑም ተነግሯል።

ሁለቱ ጥንዶች ፒተር ስሚርለስ እና ጄን ሮብሰን የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ከዚህ ቀደም ብለው ለማድረግ ያሰቡ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለማራዘም ተገደዋል።

ሆኖም ከፈረንጆቹ ገና በኃላ የፒተር የጤንነት ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲመጣ ሀኪማቸው የሰርግ ስነ ስርዓቱ በፍጥነት እንዲከወን መክሯቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ጥንዶቹ በዊልቲሸር፣ ፑተር በሚገኝ ሴደር በተሰኘ የእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ጋብቻቸውን ለመፈፀም በቅተዋል።

ሁለቱ ጥንዶች በፍቅር 26 ዓመታት ቆይተዋል።

"የመጀመሪያውን የ'ላግባሽ' ጥያቄ ያቅረበልኝ ከ 25 ዓመታት በፊት ቢሆንም 'ለምን እንጣደፋለን?' ብዬዋለው" የሚሉት አዲሷ የዕድሜ ባለጠጋ ሙሽራ "ይህ መቼም የሚሆን አይመስልም ነበር" ሲሉ ገልፀዋል።

የጥንዶቹ የጋብቻ ስነ ስርዓት ከመፈፀሙ አስቀድሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ሁኔታ በተመለከተ ምልከታ የተደረገ ሲሆን ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ መንገዶች መተግበራቸውም ተገልፃል።