ዛንዚባር 'ሥነ ምግባር የጎደለው ልብስ የሚለብሱ ጎብኝዎችን' ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ታትሟል
በታንዛኒያ ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ዛንዚባር የሚገኙ ባለሥልጣናት ጎብኚዎች "ሥነ ምግባርን የተከተለ አለባበስ በመልበስ" የአከባቢውን ባህል እንዲያከብሩ ካልሆነም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አሳስበዋል ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሌላ ሙሃመድ ሙሳ ለቢቢሲ ስዋሂሊ እንደተናገሩት አንዳንድ ጎብኚዎች በጎዳናዎች ላይ "ራቁታቸውን በሚባል ደረጃ" ይንቀሳቀሳሉ፡፡
አስጎብኚ ድርጅቶችም ደንበኞቻቸው ተገቢ የሆነ አለባበስ ካልተከተሉ በትንሹ 700 ዶላር እንደሚቀጡ ተናግረዋል፡፡
ሬስቶራንቶች እና ሆቴሎችም ጎብኚዎች "የሥነ ምግባር ደንባቸውን" እንዲያከብሩ መምከር አለባቸው ብለዋል፡፡
"ጎብኚዎቹን ማስተማር ድርሻቸው ስለሆነ ህጎችን ከጣሱ እኛም እንቀጣቸዋለን" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም "ግባችን ቱሪስቶችን መቀጣት ሳይሆን ሰዎች በአክብሮት እንዲለብሱ ማረጋገጥ ነው" ብለዋል፡፡
ዛንዚባር ለምዕራባውያን ቱሪስቶች ተወዳጅ የመዳረሻ ቦታ ናት፡፡








