ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትዊተር ያለፈው ዓመት በትርፍ የተንበሸበሽኩበት ነበር አለ
ትዊትር የፈረንጆቹ 2020 የመጨረሻ ሩብ ዓመት ልዩ ነበር ብሏል። ልዩ ባለው ዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማካበቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጃክ ዶርሲ ገልጿል።
ትዊተር በ2019 የመጨረሻ ሩብ ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ2020 ትርፉ በ28 በመቶ ማደጉ ታውቋል። ይህም ወደ ገንዘብ ሲቀየር 1.29 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል።
2021 ከገባ በኋላ ደግሞ ትዊተር አንድ ግዙፍ ሰውን ከትዊተር አሰናብቷል፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን። ተንታኞች የዚህኛው ሩብ ዓመት የትዊተር ገቢ በትራምፕ ስንብት ምክንያት ሊያሽቆለቁል ይችላል እያሉ ነው።
የትዊተሩ አለቃ ጃክ ዶርሲ ግን "ከየትኛውም ርዕሰ ጉዳይም ሆነ ከየትኛውም ግለሰብ ገጽ በላይ እኛ ግዙፍ ነን" በማለት ትንታኔውን ዋጋ ቢስ ለማድረግ ሞክሯል።
በእርግጥ ከአሁን በፊትም ተንታኞች ጠብቀውት የነበረውን ትርፍ በዓመቱ አራተኛው ሩብ ላይ ትዊተር ማሸነፍ ችሏል። በአንጻሩ የትዊተር ተጠቃሚዎችን ቁጥርን ግን ማሳደግ አልቻለም።
ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ በዋሺንግተን ዲሲ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች አመጽ መቀስቀሳቸውን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ በቋሚነት ከትዊተር መታገዳቸው ይታወሳል።
በምላሹ ጃክ ዶርሲ ተጠቃሚዎች ከ6 ሺ በላይ አዳዲስ ርዕሰ ጉዳዮችን መከታተል ይችላሉ ብሏል።
"80 በመቶ የሚሆነው የትዊተር ተከታይ ከአሜሪካ ውጭ ነው" በማለትም የትራምፕን ስንብት ረብ የለሽነት አብራርተዋል።
"ያለን ዓለም አቀፍ አገልግሎት ነው። ደግሞም ትዊተር እንዲመነደግ ዜና እና ፖለቲካ ላይ የሙጥኝ የምንል አይደለንም" ሲል ገልጿል።
በ2020 ሦስተኛው ሩብ ዓመት የትዊተር አጠቃላይ ዕለታዊ ንቁ ተጠቃሚ በ5 ሚሊዮን በማደግ 192 ሚሊዮን ደርሷል። ተንታኞች 193.5 ሚሊዮን ይደርሳል ብለው ያስቀመጡትን ግብ ባያሳካም የ26 በመቶ እድገት ግን አሳይቷል።
የትዊተር የማስታወቂያ ገቢ በየዓመቱ በ31 በመቶ በማደግ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።