ቻይና አውስትራሊያዊቷን ጋዜጠኛ በስለላ ወንጀል ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያዊቷ ጋዜጠኛ ቺንግ ሊ ብሔራዊ ሚስጥርን ለሌላ አገር በማሳለፍ በቻይና ክስ ተመሠረተባት።
በቻይና ለሦስት ወራት ታግታ የነበረቸው ጋዜጠኛዋ በቻይና የስለላ ክስ እንደሚመሰረትባት የአውስትራሊያ መንግሥት ይፋ አድርጓል።
ጋዜጠኛዋ ከመታሰሯ በፊት የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ ሲጂቲኤን ባልደረባ ነበረች።
ነሐሴ ላይ ከታገተች በኋላ ባለፈው ሳምንት ይፋዊ ክስ ተመስርቶባታል።
አውስትራሊያ የጋዜጠኛዋን እስር በተመለከተ ለቻይና ቅሬታዋን ገልጻለች።
"መሠረታዊ ሕጎች እንዲከበሩ፣ የፍርድ ሂደቱ ፍትሐዊ እንዲሆን፣ ቺንግ ሊ ሰብዓዊነት በተሞላው መንገድ እንድትያዝ እንጠይቃለን" ሲሉ የአውስትራሊያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማሪስ ፔን ተናግረዋል።
ጋዜጠኛዋ ለምን ታሰረች?
ትውልደ ቻይናዊቷ ጋዜጠኛዋ ዜግነቷ የአውስራሊያ ነው። ላለፉት ጥቂት ዓመታት ቢጂንግ ውስጥ ሠርታለች።
ሁለት ልጆቿና የተቀረው ቤተሰቧ አውስትራሊያ ይኖራሉ።
ነሐሴ ላይ ድንገት ከቴሌቭዥን ጠፍታ ቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ያለችበትን ማወቅ አልቻሉም። ትሠራበት የነበረው ሲቲጂኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ ከገጹ ላይ የጋዜጠኛዋን ሥራዎች በአጠቃላይ አውርዶም ነበር።
ከዚያም ቻይና ጋዜጠኛዋን እንዳገተቻትና ባልታወቀ ቦታ በብሔራዊ ደህንነት አባላት ስር እንዳለች ተገለጸ።
የጋዜጠኛዋ የእህት ልጅ ሉዊሳ ዌን "ብሔራዊ ደህንነትን የሚጎዳ ነገር ሆነ ብላ ታደርጋለች ብዬ አላስብም። ምንነቱ ባልገባት ነገር ውስጥ ገብታ እንደሆነም አናውቅም" ስትል ለአውስትራሊያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግራለች።
ጋዜጠኛዋ በተለያየ ጊዜ ምርመራ እንደተደረገባት፣ እንደታሰረችና ጤናዋም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ ወኪል ጋዜጠኛዋን በወር አንዴ እንዲጎበኙ ተፈቅዶላቸዋል።
ቻይና እና አውስትራሊያ
የቻይና እና አውስትራሊያ ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል። በዲፕሎማሲና በንግድ ዘርፍም እየተወዛገቡ ነው።
ተንታኞች እንደሚሉት፤ በሁለቱ አገራት ውጥረት ሳቢያ የአውስትራሊያ ባለሥልጣኖች ዜጎቻቸውን ከእስር ለማስለቀቅ ከቤጂንግ ጋር መደራደር አልቻሉም።
ቻይና ብዙ የአውስትራሊያ ጋዜጠኞችን አባራለች፤ በቁጥጥር ስርም አውላለች።
ቺንግ ሊ ከታሰረች በኋላ ሁለት ቻይና ውስጥ የነበሩ አውስትራሊያውያን ጋዜጠኞች ሸሽተው ወጥተዋል።
የኤቢሲ ዘጋቢ የሆነው ቢል ቢርትልስ ከቻይና ከመውጣቱ በፊት ፖሊሶች ስለ ቺንግ ሊ እንዲሁም ስለተለያዩ ጉዳዮች ጠይቀውት እንደነበር ገልጿል።
ጥቅምት ላይ ቻይና የብሉምበርጓን ጋዜጠኛ ሀዜ ፋን በቁጥጥር ስር አውላ ነበር።
ቻይናዊቷ ጋዜጠኛ የታሰረችው ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ጥለሻል ተብላ ነው።
ብሉምበርግ የጋዜጠኛዋ ደህንነት እንደሚያሳስበው ገልጾ ስለ እስሯ መረጃ እንዲሰጠው ጠይቋል። ብሉምበርግና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የሚዲያ ባልደረቦች ጋዜጠኛዋ እንድትለቀቅ አሳስበዋል።
ያንግ ሄንጁን የተባለ በትውልድ ቻይናዊ የሆነ አውስትራሊያዊ ጸሐፊ ከታሰረ ሁለት ዓመት ተቆጥሯል። በስለላ ክስ ቢመሰረትበትም ክሱ የሐሰት ነው ብሏል።
ጸሐፊው በተደጋጋሚ ምርመራ እንደተደረገበትና እግሩ ታስሮ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ በመጥቀስ አውስትራሊያ ቅሬታ አሰምታለች።












