ባይደን ከኢራን ጋር ለመነጋገር ብለው ማዕቀብ እንደማያነሱ ገለጹ

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ኢራን እአአ በ2015 የተፈረመውን የኒውክሌር ስምምነት ካልተገበረች ማዕቀብ እንደማያነሱላት ተናገሩ።

አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ከኢራን ጋር ለመነጋገር ስትል እንደማታነሳ ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የኢራኑ መሪ አያቶላ አሊ ካምኒ በበኩላቸው ኢራን ስምምነቱን የምታከብረው አሜሪካ ማዕቀቡን ስታነሳላት ነው ብለዋል።

2015 ላይ የኢራንን የኒውክሌር ምርት የሚገድብ ስምምነት ተፈርሞ ነበር። የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን በ2018 ከስምምነቱ አስወጥተዋል።

ስምምነቱ ሲፈረም ላልተው የነበሩ ማዕቀቦችን ትራምፕ በድጋሚ አጥብቀውም ነበር።

ኢራን ማዕቀቦቹ እንደ አዲስ መጣላቸውን ተከትሎ ከስምምቱ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች መፈጸም ጀምራለች።

ኒውክሌርን ለሰላማዊ ተግባር ነው የማውለው የምትለው ኢራን የተጣራ ዩናንየም ምርቷን እያሳደገች ነው። የተጣራ ዩናንየም የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት ይውላል።

ስምምነቱ ለምን ፈረሰ?

ኢራን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩስያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በ2015 የኒውክሌር ስምምነት ፈርመው ነበር። በስምምነቱ መሠረት ቴህራን የምታበለጽገውን ዩራንየም እንደምትቀንስና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የምርት ሂደቱን እንዲከታተሉ እንደምትፈቅድ ተገልጿል።

ኢራን እነዚህን እርምጃዎች ከወሰደች በምላሹ ማዕቀቦች እንደሚነሱላት ቃል ተገብቶም ነበር።

ሆኖም ግን ትራምፕ አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጥተው ኢራን አዲስ ስምምነት እንድትፈርም ጫና ለማሳደር ሞክረዋል።

ኢራን በአዲሱ የትራምፕ እቅድ አልስማማም ብላ ዩራንየምን በ20% ጥራት ወደ ማምረት እንደምትመለስ አስታውቃለች። የጦር መሣሪያ መሥራት የሚቻለው 90% የምርት ጥራት ላይ ሲደረስ ነው።

ባይደን ኢራንን ወደቀደመው ስምምነት ለመመለስ ሲሉ ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀቦችን ያነሱ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ "በፍጹም ማዕቀብ አላነሳም" ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢራን ግን ወደቀደመው ስምምነት ለመመለስ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ የማዕቀቦችን መነሳት ያካትታል።

የኢራኑ መሪ በብሔራዊ ቴሌቭዥን "ሁሉንም ማዕቀቦች ያንሱ። ከዚያ ወደ ስምምነቱ እንደመለሳለን" ሲሉ ተደምጠዋል።