ኢራን ፡ ባለፈው ሳምንት የተገደሉት ዋነኛው የኢራን የኑክሌር ሳይንቲስት ተቀበሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን ባለፈው ሳምንት ለተገደሉት ጉምቱ የኒውክሌር ሳይንቲስቷ ሞህሰን ፋክሪዛዴህ የቀብር ሥነ-ሥርዓት አከናውናለች።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አሚር ሃታሚ ንግግር ባሰሙበት ወቅት የሳይንቲስቱን ሞት ለመበቀል ዝተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ሳይንቲስቱ የጀመሩትን እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
አንድ ሌላ ባለሥልጣን በቀብሩ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ገዳዮቹ 'ኤሌክትሮኒክስ' ተጠቅመው ነው የገደሉት እንጂ በሥፍራው አልነበሩም ብለዋል።
እስራኤል የሳይንቲስቱን ግድያ ተከትሎ የቀረበባትን ክስ በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።
ነገር ግን ሳይንቲስቱ ምስጢራዊ የኒውክሌር ፕሮግራም ያስተባብሩ እንደነበር አምናለች።
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ አሁንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ እንዳለ ትናገራለች።
የሳይንቲስቱ የስንብት ሥነ-ሥርዓት ቴህራን በሚገኘው የመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተካሄደ በኋላ አስከሬኑ ወደ ሰሜናዊ የከተማዋ ክፍል ተወስዷል።
የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በባንዲራ የተሸፈነ የሬሳ ሳጥን በወታደሮችና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ታጅቦ ሲሄድ አሳይቷል።
የደኅንነት ሚኒስትሩ ሞሐመድ አላቪ፣ የአብዮታዊ ጥበቃው አዛዥ ጀኔራል ሁሴን ሳላሚ እንዲሁም የኒውክሌር ፕሮግራሞች ኃላፊ አሊ አኽባር ሳሌህ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የአብዮታዊው ዘብ አዛዥ ጀኔራል ሁሴን "ጠላቶቻችን እንዲያውቁ የምንፈልገው ገዳዮቹን እንደምንደርስባቸው ነው" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሳይንቲስቱ ፋክሪዛዴህ ያከናወኑት ተግባር ሥራ እየተነሳ ተወድሰዋል።
የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሳይንቲስቱ ላይ የግድያ ሙከራ ሊኖር እንደሚችል መረጃው ቢደርሰንም ቴክኖሎጂያዊ በሆነ መንገድ የተፈፀመ ስለሆነ ግድያውን ማስቀረት አልቻልንም ብለዋል።
ከአብዮታዊ ጥበቃው ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነግርለት ኢራን ፋርስ ኒውስ የተሰኘው የዜና ወኪል ሳይንቲስቱ የተገደሉት በርቀት መቆጣጠሪያ [በሪሞት ኮንትሮል] ቁጥጥር በሚደርግለት የጦር መሣሪያ ነው ሲል ዘግቧል።
ፕሬስ ቲቪ ደግሞ ውስጥ አዋቂዎች ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ሳይንቲስቱ የተገደለኩበት መሣሪያ የእስራኤል ጦር መሣሪያ ማምረቻ ምርት መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ተገኝተዋል።
ነገር ግን ባለፈው አርብ የኢራን መከላከያ ሚኒስቴርና የዓይን እማኞች ሳይንቲስቱን የገደሉት ሰዎች ከጠባቂዎቻቸው ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።
የእስራኤል ደኅንነት ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን ሰኞ ዕለት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሰውዬውን ማን እንደገደላቸው እንደማይውቁ ተናግረዋል።
ነገር ግን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ስማቸውን ያልተጠቀሰ አንድ የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣን "በፋክሪዛሄድ የሚመራው የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ለዓለም ስጋት ነው" ብለዋል ሲል ዘግቧል።
እስራኤልና ምዕራባውያን ፋክሪዛሄድ የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም አድራጊ ፈጣሪ ናቸው ብለው ያምናሉ።












