የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸውን አምነው ካዱ

ታትሟል

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ካመኑ ከሰዓታት በኋላ ቃላቸውን መልሰው አስተባብለውታል።

ትራምፕ "(ባይደን) ምርጫውን አሸንፏል" ብለው የጻፉት በትዊተር ሰሌዳቸው ነው። "አሸንፏል" የሚለውን ቃል ሲጠቀሙም ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ይህንን ቃል በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ካሰፈሩ ከ1 ሰዓት በኋላ ግን "ጆ ባይደን ያሸነፈው የተጭበረበረውን ምርጫ ነው። በፍጹም መሸነፌን አምኜ አልቀበልም" ብለዋል።

ትራምፕ በተሸነፉባቸው የአሜሪካ ግዛቶች ቢያንስ በዋና ዋናዎቹ አካባቢዎች የክስ መዝገብ አስከፍተዋል። ጠበቆቻቸው ቀን ተሌት ምርጫው ፉርሽ እንዲባል እየወተወቱ ነው። ሆኖም እስካሁን አንድም የረባ ነጥብ ማስቆጠር አልቻሉም።

አርብ ዕለት የምርጫ አስፈጻሚዎች ይህ ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ "ተአማኒ፣ ነጻና ፍጹም ተቀባይነት ያለው" ሲሉ ገልጸውታል። እስከአሁን ባለው ሂደትም ምርጫው ስለመጭበርበሩ የሚያሳይ አንዳችም የረባ ማስረጃ ሊገኝ አልቻለም።

አሁን በሁሉም ግዛቶች ቆጠራ ተጠናቆ ባይደን ከ50 ግዛቶች በድምሩ 306 የውክልና ድምጽ ማግኘታቸው ተረጋግጧል። ለማሸነፍ አስፈላጊው የውክልና ድምጽ ግን 270 ብቻ መሆኑ ይታወቃል።

ባይደን ከሚያስፈልጋቸው የማሸነፍያ ነጥብ በብዙ የራቀ ውጤት በማስመዝገባቸው ትራምፕ ተጭበርብሯል በሚሏቸው ግዛቶች ዳግም ቆጠራ ተደርጎ ውጤቱ ቢቀለበስ ለፕሬዝዳንትነት የሚያበቃና አሸናፊ የሚያደርግ ቁጥር የማግኘታቸው ነገር ሩቅ ነው።

በመራጭ ተወካዯች ቁጥር ሳይሆን ብዙ ሕዝባዊ ድምጽ በማግኘትም ቢሆን ባይደን ከትራምፕ በላይ የ5 ሚሊዮን ሰዎችን ድምጽ አግኝተዋል። በአሜሪካ የምርጫ አሰራር ግን ብዙ የሕዝብ ድምጽ ያገኘ የፕሬዝዳንትነት ውድድሩን ያሸንፋል ማለት አይደለም።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አወዛጋቢው ትራምፕ ውጤቱን መቀበል ተናንቋቸዋል።

አርብ ዕለት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀብለው ጆ ባይደንን እንኳን ደስ ያለህ ይላሉ ወይ በሚለው ጥያቄ ዙርያ ውሃ ቸልሰውበታል።

"ማን ያውቃል በሚቀጥሉት ዓመታት ሥልጣን ላይ ማን እንደሚቆይ" ሲሉ ጥርጣሬን አራግበዋል።

በትዊተር ሰሌዳቸው በድጋሚ ብቅ ብለውም፣ "እሱ ያሸነፈው በሐሳዊ የዜና ማሰራጫዎች ድምጽ ነው፤ በፍጹም መሸነፌን አልቀበልም" ብለው ጽፈዋል።

ይህን ንግግራቸውን ተከትሎ የትራምፕ ደጋፊዎች በዋሺንግተን ዲሲ አደባባይ በመውጣት ረብሻና ሁከት ፈጥረዋል። በዚህም መጠነኛ ጉዳት ደርሷል።

ጆ ባይደን እስከአሁን ድረስ የአገሪቱን ምስጢሮች በተመለከተ ልዩ የደኅንነት መግለጫ እያገኙ አይደለም። ተመራጭ ፕሬዝዳንት በዚህ ወቅት አሜሪካ በሁሉም ረገድ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለች የሚያብራሩ ሚስጢራዊ መረጃዎች ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሊቀርቡለት ይገባ ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ አሜሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየታመሰች ትገኛለች። በቀን ከ180 ሺህ ሰዎች በላይ ዜጎች በተህዋሲው እየተያዙ ሲሆን አርብ ዕለት ብቻ 1 ሺህ 400 አሜሪካዊያን ሕይወታቸውን እንደዋዛ አጥተዋል።