የፖሊስ አባሉ በአውራ ዶሮ ተገደለ

ታትሟል

የፊሊፒንስ ፖሊስ አባል ሕገ-ወጥ የአውራ ዶሮ ፍልሚያን ለማስቆም በተደረገ ዘመቻ ላይ በአውራ ዶሮ ተገደለ።

ፊሊፒንስ ውስጥ አውራ ዶሮዎች ሲፋለሙ እግራቸው ላይ የብረት ምላጭ ማሰር የተለመደ ነው።

አውራ ዶሮው እግሩ ላይ በታሰረው ምላጭ ክሪስቲን ቦሎክ የተባለው የፖሊስ አባል ከቆረጠው በኋላ ነው የፖሊሱ ሕይወት ያለፈው።

ምላጩ የግራ ጭኑን ላይ የደም ቧንቧው ቆርጦታል። ከጉዳቱ በኋላ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሆስፒታል የደረሰው ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

የአውራ ዶሮዎች ፍልሚያ ፊሊፒንስን ጨምሮ በበርካታ አገራት ተወዳጅ ሲሆን ብዙ ሰዎችም በውጤቱ ላይ ተመሥርተው ለመወራረድ ይሰባሰባሉ።

በሌሎች አገራት ግን አውራ ዶሮዎን ማጣላት ሕገ-ወጥ እና ኢ-ሰብዓዊነት ተደርጎ ይቆጠራል።

ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ፊሊፒንስ ውስጥ የአውራ ዶሮዎች ፍልሚያ በሕግ ታግዷል።

እንደ ፊሊፒንስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ፍቃድ ላላቸው ብቻ እሁድ፣ በብሔራዊ በዓላት ቀን እና አከባቢያዊ ፌስቲቫሎች ሲከበሩ ብቻ ለሦስት ቀናት የሚረዝም የአውራ ዶሮ ፍልሚያ ይፈቀዳል።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ኮሎኔል አርኔል አፑድ አደጋውን "አሳዛኝ" እና "መግለፅ የማልችለው መጥፎ ዕድል" ሲሉ ለኤዜፍፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

"መጀመሪያ ሲነገረኝ ማመን አልቻልኩም ነበር። በ 25 ዓመታት የፖሊስ አባል ዘመን በዶሮ ምክንያት የሰው ሕይወት ሲጠፋ ይህ የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።

የፖሊስ አዛዡም ለሟች ቤተሰቦች "ጥልቅ ሀዘናቸውን" ግልጸዋል።

ሕገ-ወጥ የአውራ ዶሮ ፍልሚያውን ለማስቆም በተደረገው ዘመቻ ሦስት ሰዎች እና ሰባት አውራ ዶሮዎች መያዛቸው ተዘግቧል።

ሌሎች ሶስት ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተንቀሳቀሰ ነው።