ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኳታር ሴቶች 'በአስነዋሪ' መልኩ ተፈትሸዋል መባሉን እመረምራለሁ አለች
ኳታር በተለያዩ 10 በረራዎች ለመብረር የተዘጋጁ ሴቶች በዶሃ አየር ማረፊያ 'አስነዋሪ' ፍተሻ ተደርጎባቸዋል መባሉን አጣራለሁ አለች።
"በጣም አስነዋሪ" የተባለው ፍተሻ ሴቶቹ ላይ የተደረገው በአየር ማረፊያው መጸዳጃ ቤት ውስጥ አንዲት ጨቅላ ልጅ ተጥላ መገኘቷን ተከትሎ ነበር።
ሴቶቹ የተፈተሹት በቅርቡ ልጅ ስለመውለዳቸው የሚያመላክት ምልክት ለማግኘት ነበር ተብሏል።
ፍተሻ ከተደረገባቸው ሴቶች መካከል ቢያንስ 18ቱ የአውስትራሊያ ዜጎች መሆናቸውን የአውስትራሊያ መንግሥት አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም የአውስትራሊያ መንግሥት ሴቶቹ ለፍተሻ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ተደርገዋል፤ ይህን 'በጣም አስነዋሪ' ፍተሻን በተመለከተም የኳታር መንግሥት ማብራሪያ ይስጥ ሲል ጠይቋል።
አውስትራሊያ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ፖሊሷ መርታዋለች።
የኳታር መንግሥት ለደርጊቱ ይቅርታ ጠይቆ ጨቅላዋ ደህንነቷ ተጠብቆ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ጨቅላዋ በፕላስቲክ ተሸፍና መጣሏን እና ወላጅ እናቷን ለማግኘት የተደረገ ጥረት መሆኑንም የኳታር መንግሥት አስታውቋል። ጨምሮም ፍተሻወን ማድረግ ያስፈለገው ጥፋተኛውን ሰው ለመለየት ነው፤ በዚህ ፍተሻ የተበሳጩ ሰዎችን ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሏል።
የምርመራው ውጤት ሲጠናቀቅ ውጤቱን ለሌሎች መንግሥታትም አሳውቃለሁ ብሏል የኳታር መንግሥት።
ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ከተደረጉት አንዷ ኪም ሚልስ ለጋርዲያን እንደተናገሩት፤ ወደጨለማ የመኪና ማቆሚያ ተወስደዋል። በቦታው ሦስት አምቡላንሶች ለሴቶቹ ምርመራ ለማድረግ እየጠበቁ ነበር።
60ዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙት ኪም ሳይመረመሩ መቅረታቸውንም አስረድተዋል። ባይመረመሩም ግን ያዩት ነገር አስቀያሚ እንደነበር አክለዋል።
"እግሬ እየተንቀጠቀጠ ነበር። የሆነ ቦታ ይወስዱኛል ብዬ ፈርቼ ነበር። ምን እየተካሄደ እንደነበር ለምን አልነገሩንም? በጣም አሰቃቂ ነበር። ወጣቶቹ ሴቶች ምን እንደተሰማቸው ማሰብ ይከብደኛል" ብለዋል።
ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ዎልፍጋንግ ባቤክ ለአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደተናገረው፤ ሴቶቹ በጣም ተቆጥተው ወደ አውሮፕላኑ ተመልሰዋል።
"ብዙዎቹ በጣም ተበሳጭተው ነበር። አንድ ወጣት ሴት እያለቀሰች ነበር" ብሏል።