ዲዝኒ ዘረኛ ፊልሞች ላይ የሚለጥፈውን ማስጠንቀቂያ አሻሻለ

ታትሟል

ዲዝኒ እድሜ ጠገብ የልጆች ፊልሞች ዘረኛ ይዘት እንዳላቸው ማስጠንቀቂያ መለጠፍ ከጀመረ ዓመት ሆኖታል። አሁን ደግሞ ማስታወቂያው የበለጠ ጠንካራ ሆኖ መሻሻሉ ተገልጿል።

በዲዝኒ ፕላስ የሚሰራጩት እንደ ዳምቦ፣ ፒተር ፓን እና ጀንግል ቡክ ያሉ ፊልሞች ውስጥ መድልዎ እንደሚታይ ይጠቁማል።

"ይህ ፕሮግራም አንድ ማኅበረሰብን በአሉታዊ ሁኔታ ይሥላል። መድልዎው ያኔም አሁንም ስህተት ነው" ይላል ማስጠንቀቂያው።

ፊልሞቹን ከማስወገድ ይልቅ ምን ያህል ጎጂ እንደሆኑ አምኖ፣ ከስህተት መማር እና አካታችነትን የተመለከተ ውይይት እንዲያጭሩ ማድረግ እንደሚፈልግ ዲዝኒ አስታውቋል።

ቢጫ ቀለም የተቀባ ድመት በቾፕስቲክ ፒያኖ ሲጫወት የሚያሳየው 'ዘ አሪስቶክራትስ' እና ቀደምት አሜሪካውያንን 'ሬድስኪንስ' በማለት የሚያጥላላው 'ፒተር ፓን' ማስጠንቀቂያ ከተለጠፈባቸው መካከል ናቸው።

ዘረኛ ፊልሞች ላይ ማስጠንቀቂያ የለጠፈው ዲዝኒ ብቻ ሳይሆን ዋርነር ብሮስም ነው።

"እነዚህ ካርቱን ፊልሞች የአሁኑን ማኅበረሰብ አይወክሉም። ቀድሞ በተሠሩበት መንገድ የቀረቡት ያኔ የነበረውን መድልዎ ላለመካድ ነው" ይላል ማስጠንቀቂያው።

ማስጠንቀቂያ የተለጠፈባቸውየዲዝኒ የልጆች ፊልሞች

ሌዲ ኤንድ ዘ ላምፕ (1955): ሲ እና አም የተባሉት ድመቶች ጸረ እስያውያን ናቸው። የሜክሲኮ፣ የሩስያና ሌላም አገሮች ውሾች ገጸ ባህሪዎች በየአገራቸው የቋንቋ ቅላጼ እንዲናገሩም ተደርጓል።

ዘ አሪስቶክራትስ (1970): ሹን ጎን የተባለ ድመት ገጸ ባህሪ በነጭ ተዋናይ መተረኩ ዘረኛ እሳቤ ነው።

ዳምቦ (1941): ዳምቦን መብረር የሚያስተምሩት አሞራዎች በጣም በተጋነነ እና ዘረኛ በሆነ መንገድ የጥቁር ድምጽ ይጠቀማሉ። ዋናው አሞራ ጂም ክሮ ይባላል። ይህም በደቡብ አሜሪካ ያለ መድሏዊ መጠሪያ ነው።

ጃንግል ቡክ (1968): ሊዊ የተባለው ጦጣ ገጸ ባህሪ የቋንቋ ውስንነት ያለበት ሲሆን፤ ጃዝ የሚጫወት ሰነፍ ተደርጎ ተስሏል። ጥቁር አሜሪካውያንን በተሳሳተ መንገድ የሚሥልም ነው።

ፒተር ፓን (1953): በፊልሙ ቀደምት ማኅበረሰብ ዘረኛ በሆነ መንገድ 'ሬድስኪን' ይባላሉ። ፒተር ፓንና ታዳጊዎቹ ገጸ ባህሪዎች ራሳቸው ላይ ጥምጣም አስረው ሲደንሱ የሚታየውም፤ የማኅበረሰቡን ባህል ያጥላላል።

ሶንግ ኦፍ ዘ ሳውዝ (1946): ከዲዝኒ አወዛጋቢ ፊልሞች አንዱ ነው። አንክል ረሙስ የተባለ በግዞት እርሻ ላይ የሚሠራ ገጸ ባህሪ፤ በባርነት የተያዙ ሰዎች ደስተኛ እንደነበሩ የተሳሳተ ምልከታ ይሰጣል።