ምርጫ፡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መደበኛ ሥራቸዉ ለመመለስ ዝግጁ ናቸው ተባለ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መደበኛ ሥራቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ሐኪሞቻቸው ተናገሩ።

በኮሮናቫይረስ የተያዙት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮቪድ-19 ሕክምናቸውን መጨረሳቸውን በመግለጽ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ወደ ሥራቸው መመለስ እንደሚችሉ ሐኪማቸው ተናግረዋል።

ዶ/ር ሼን ኮንሌይ፤ ፕሬዝዳንቱ ለወሰዷቸው መድሃኒቶች ጥሩ ምላሽ መስጠታቸውንና የጤና ሁኔታቸው አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕም ይህንን የሐኪማቸውን አስተያየት ተከትሎ ዛሬ ሌላ የኮቪድ-19 ምርመራ ካደረጉ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለመጨረሻ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ ሥራቸዉ መመለስና ህዝባዊ ክንውኖች ላይ መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።

ፕሬዝዳንቱ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ከተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን ጋር በቀጥታ በቴሌቪዥን ከሚካሄደው የምርጫ ክርክር ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

የክርክሩ አዘጋጆች የትራምፕን በኮቪድ-19 መያዝ ካወቁ በኋላ በቴሌቪዥን የሚካሄደው የምረጡኝ ክርክሩ 'ቨርቹዋል' በሆነ መንገድ በርቀት ይከናወናል ማለታቸውን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ " በቨርቹዋል ለሚደረግ ክርክር ጊዜዬን አላባክንም" ብለዋል።

የግል ሀኪማቸዉ ዶ/ር ሼን ኮንሌይ፤ አሁን ላይ ፕሬዝዳንቱ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የሚሰጣቸዉን ህክምና ማጠናቀቃቸዉንና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

ፕሬዚደንቱ ለ24 ሰዓታት ያህል የኮቪድ-19 ምልክት ያልታየባቸው ሲሆን ለተከታታይ አራት ቀናትም ትኩሳት እንዳልነበራቸው የግል ሐኪማቸው ሼን ኮንሊይ ተናግረዋል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ደህንነት ይሰማቸው እንደነበር ገልፀው፤ "ይህ በፈጣሪ መባረክ ነው" ብለዋል።

በንግግራቸውም ሁሉም አሜሪካዊያን ለእርሳቸው የተሰጠውን መድሃኒት እንዲያገኙ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

በመሆኑም በወቅቱ በመድሃኒት አምራቹ ሬጀኔሮን የተመረተውን መድሃኒት በነፃ ለመስጠት ፕሬዚደንቱ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዚደንቱ አክለውም ባለፈው ሳምንት የተሰጣቸው በሙከራ ላይ ያለው የሰውነት በሽታ መከላከል አቅምን የሚጨምረው አንቲቦዲ ማገገሚያ ብቻ ሳይሆን ፈዋሽ ነው በማለትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መጠን [ዶዝ] ያለው መድሃኒት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጅ ድርጅቱ የሚያመርተው መድሃኒት በፌደራል የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የተረጋገጠ አይደለም።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ኮሮናቫይረስ በፕሬዝዳንት ትራምፕ አንደበት!
ኮሮና
Banner