ሙስና፡ አፍሪካ 836 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ ወጥቶባታል- ሪፖርት

ታትሟል

አፍሪካ በህገወጥ መንገድ ወደተለያዩ አገራት የተሻገረባት የገንዘብ መጠን 836 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት አሳይቷል።

አፍሪካ ይህንን ያህል መጠን ገንዘብ ያጣችው ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ፣ አልማዝና ፕላቲኒየም የመሳሰሉ ማእድናት ጋር በተገናኘ ከሌሎች አገራት ጋር በምታደርገው የውጪ ንግድ በኩል ነው።

ይህም ከሙስና፣ ሌብነትና ግብር ማጭበርበር ጋር የተያያዘ ነው።

ሪፖርቱን ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግድና ልማት ((UNCTAD) ሲሆን የአስራ አምስት አመታት መረጃንም አጠናቅሬያለሁ ብሏል።

አህጉሪቷ ያለባት ብድር 770 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ከሁለት አመት በፊት ያለውን መረጃ ዋቢ ያደረገው ሪፖርት አህጉሪቷ ከተሻገረባት መጠንም ጋር ሲወዳደር "የአለም ንፁህ አበዳሪ ያደርጋታል" ብሏል።

"እንዲህ ባለ ህገወጥ መንገድ የገንዘብ ዝውውር አህጉሪቷም ሆነ ህዝቧ የወደፊቱን እያጡ ነው። ይህ ሁኔታ ግልፅነት፣ ኃላፊነት የጎደለው ማሳያ ሆኗል፤ አህጉሪቷም ያሏት ተቋማትን እምነት የሸረሸረ ነው" በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግድና ልማት ዋና ፀሃፊ ሙኪሳ ኪቱዩ ተናግረዋል።

የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ መሆንም የአፍሪካ መንግሥታት በጤና ስርአቱ፣ ትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖም እንደሚያሳርፍ ተጠቅሷል።

"እንዲህ አይነት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሙስና የአፍሪካ ልማት እክል ሆኗል። በከፍተኛ ሁኔታም አገሪቷ በውጭ ምንዛሬ ድርቅ እንድትመታ ምክንያት ሆኗል። በአገራቱ ውስጥ ያለው የምርት አቅርቦት እንዲያሽቆለቁል ፣ የንግዱና አጠቃላይ ምጣኔ ኃብቱ እንዲጎዳና ድህነትና አለመጣጠን እንዲከፋ አድርጎታል" ብለዋል ዋና ፀሃፊው።