ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍርድ ቤት፡ የመዋዕለ ሕጻናትን ተማሪዎች መረዘችው ቻይናዊት ሞት ተፈረደባት
በቻይና 25 የመዋዕለ ህጻናትን ተማሪዎችን የመረዘችውና አንድ ህጻንን የገደለችው መምህርት የሞት ፍርድ እንደተፈረደባት የቻይና መገናኛ ብዙኀን ዘገቡ።
ዋንግ ዩን በቁጥጥር ስር የዋለችው ባለፈው ዓመት ትሰራበት በነበረው መዋዕለ ህጻናት የሚማሩ ተማሪዎች ቁርሳቸውን በልተው በመታመማቸው ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ከተደረገ በኋላ ነው።
ይህች መምህርት በአንድ ባልደረባዋ በመናደዷ እና ቂም በመቋጠሯ ልጁን ለመጉዳት በሚል የተማሪዎቹ ምግብ ውስጥ ሶዲየም ናይትሬት መጨመሯ ተገልጿል።
ይህም ድርጊቷ የዋንግን ድርጊት "ጨካኝ እና አረመኔ" አሰኝቷታል።
ይህ ባለፈው ዓመት የተፈጠረ ክስተት ቻይናውያንን ሲያስደነግጥ በመላው ዓለም የዜና ሽፋን አግኝቶ ነበር።
ተማሪዎቹ ቁርሳቸውን ከተመገቡ በኋላ 23 ሕጻናት ማስመለስ መጀመራቸው እና ራሳቸውንም መሳታቸው ተገልጿል።
ፖሊስም መምህርቷ መርዛቸዋለች የሚል መረጃ ከደረሰው በኋላ ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል።
ሰኞ ዕለት የዢያኦዞኦ ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዋ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ የሞት ፍርድ እንደፈረደባት ግሎባል ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።
ፍርድ ቤቱ መምህርቷ " ከሌላ መምህርት ጋር በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ከተነጋገሩ በኋላ የመምህራኖቹ ልጆች ምግብ ላይ ናይትሬት ጨምራባቸዋለች" ማለቱን የቻይና መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
ሶዲየም ናይትሬት ስጋ እንዳይበላሽ ለማድረግ የሚጨመር ሲሆን ከተገቢው በላይ ሲሆን ግን መርዛማ ነው።
ፍርድ ቤቱ አክሎም መምህርቷ ሰዎችን ስትመርዝ መጀመሪያ ጊዜዋ አይደለም በማለት፣ ከዚህ ቀደም ናይትሬት ከኦንላየን ገበያ ላይ ገዝታ ባለቤቷን መመረዟንና መጠነኛ ጉዳት እንዳጋጠመው ተናግሯል።
ከሞተው ልጅ በስተቀር ስለተቀሩት ህጻናት የተሰማ ዝርዝር መረጃየለም።
ጋዜጣው አክሎም ፍርድ ቤቱ የዋንግን ድርጊት "ጨካኝ አረመኒያዊነት የሞላበት፣ እንዲሁም ድርጊቷ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ በጽኑ ቅጣት ልትቀጣ ይገባል" ስለማለቱ ዘግቧል።
በቻይና የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሚሆነው በጥይት ተተኩሶ ካልሆነም መርፌ በመውጋት ነው።