ኮሮናቫይረስ: ብራዚል ቻይና ሰራሹን የኮሮናቫይረስ ክትባት በታህሳስ እጀምራለሁ አለች

የኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአለም አቀፍ ደረጃ በኮሮቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቃችው ብራዚል በሌሎች አገሮች ቁጥሩ ቢወርድም በብራዚል ግን በየቀኑ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ነው።

በአሁኑ ሰዓትም የአገሪቱ ፖለቲከኞች ህዝባቸውን ከኮሮናቫይረስ ህመም ለመከላከል ከተለያዩ የክትባት አምራቾች ጋር ስምምነት ለመፈፀም እየጠየቁ ሲሆን ቻይና ሰራሹን ክትባትም በታህሳስ እንጀምራለን ብለዋል።

በዚህ ሳምንት ረቡዕ በአገሪቷ ውስጥ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆነቸው የሳኦ ፖሎ ከተማ አስተዳዳሪ ቻይና ሰራሹን ክትባት ታህሳስ ላይ ለመጀመር እቅድ ተይዟል ብለዋል።

ጆዋዎ ዶሪያ እንዳሉት አምስት ሚሊዮን መጠን ያለው ሲኖቫክ የተሰኘው ክትባት በሚቀጥለው ወር ወደ ከተማዋ ይገባል ብለዋል። መላው ብራዚል እስከ የካቲት ድረስ እንደሚከተብም ተስፋ አድርገዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉትም ሲኖቫክ የተሰኘው ክትባት ለ50 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ቻይናውያን መሰጠቱን ተከትሎ ደህንነቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ማሳያና አበረታች ነው ብለውታል። ክትባቱ በብራዚል ባለስልጣናት ፈቃድ ካገኘ በመላው አገሪቷም ይሰራጫል ተብሏል። ለአሁኑ ግን ሳኦ ፖሎ ክትባቱን በታህሳስ ትጀምራለች።

እስካሁን ባለው መረጃ በብራዚል በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4.6 ሚሊዮን ሲሆን 138 ሺህ 977 ዜጎቿንም አጥታለች።

በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ያህል ክትባቶች በሙከራ ላይ ሲሆን በርካታ የምርምር ማዕከሎችም የአለም ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ለመግታትም ቀን ተሌት እየተሯሯጡ ነው።

ሆኖም በርካታ የዘርፉ ልሂቃን እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክትባት በሰፊው አቅርቦት ላይ የሚውለው በያዝነው አመት ግንቦትና ሰኔ ወር ላይ ነው በማለት ሙያዊ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ኮሮና