ትራምፕ የወግ አጥባቂዋን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በእጩነት አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአያሌ ዓመታት በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ያገለገሉትን ሩት ባደር ጊንስበርግ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የወግ አጥባቂ የተባሉትን ኤሚ ኮኒ ባሬትን በእጩነት አቅርበዋል።
ኤሚ ኮኒ ባሬትን "ከፍተኛ ስኬትን የተጎናፀፈች ሴት" በማለትም ትራምፕ አሞግሰዋቸዋል።
በህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላትም መፅደቅ ከቻለ ዳኛ ኤሚ የሊበራል ርዕዮተ አለምን ይከተሉ የነበሩትን ሩት ባደር ጊንስበርግንም ይተካሉ።
በመጪው ህዳር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዋን ለማካሄድ ሽር ጉድ እያለች ባለችው አሜሪካ የዳኛዋ እጩ መሆን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ገና ፍልሚያም ይጠብቀዋል ብለዋል።
ሆኖም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳኛ ኤሚ ለዚህ ቦታ እንደምትመጥን ባደረጉት ንግግር "የተማረችና፣ በዳኝነቷ ከፍተኛ ብቃትን ያሳየች እንዲሁም ለህገ መንግሥቱ ታማኝነትን ያሳየች" ሲሉም አሞካሽተዋታል።
የዲሞክራቱ ፕሬዚዳንት ዕጩ ጆ ባይደን በበኩላቸው ዳኛዋን ለመሾም እንዳይቻኮሉና አሜሪካ ፕሬዚዳንቷን ከመረጠች በኋላም ይደርሳል በማለትም ለህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዚደንታዊ ምርጫው ተካሂዶ ውጤቱ እስከሚታወቅ ክፍት ሆኖ መቆየት አለበት በማለትም ተሟግተዋል።
የዳኛ ኤሚ ባሬት ሹመት ከፀደቀም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያለው የወግ አጥባቂ ዳኞች አብላጫ በማሳየትም ስድስት ለሶስት ይሆናል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት የጊዜ ገደብ የሌለው የዕድሜ ልክ ሹመት ሲሆን ባሁኑ ጊዜ አምስቱን አብላጫ ወንበር የያዙት ወግ አጥባቂ ዳኞች ናቸው።
የ48 አመቷ ዳኛ ሹመታቸውም ከፀደቀ ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሾሟቸው ሶስተኛዋ የወግ አጥባቂ ዳኛ ይሆናሉ።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የጽንስ ማቋረጥ፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና የጤና አገልግሎት ጉዳይ የመሳሰከሉ ፖሊሲዎች ላይ ውሳኔያቸው ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳርፋል።
ለምሳሌም ያህል በቅርቡ በአምሳ ግዛቶች የተፈቀደው የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻና ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታይ ህዝብ ባላቸው አገራት ላይ የተጣለው የጉዞ እግድ ይጠቀሳል።












