ቬትናም የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ሞት መዘገበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት የምትመሰገነው እስያዊቷ አገር ቬትናም የመጀመሪያውን የኮቪድ -19 ሞት መዘገበች። ይህም እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ ሞት ላልመዘገበችው ቬትናም አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
በበሽታው የሞቱት የ70 ዓመቱ ግለሰብ ከሆይ አን ከምትባል ግዛት መሆናቸውንም የአገሪቷ ሚዲያ ዘግቧል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዳ ናንግ ሪዞርት አቅራቢያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከመመዝገባቸው በፊት ከሦስት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ በአገሪቷ አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልነበረም።
95 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ቬትናም፤ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ እስካሁን 509 በቫይረሱ ተይዘውባታል። ይህም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ቁጥር ነው።
በእርግጥ አገሪቷ ከሌሎች አገራት በተለየ ቫይረሱን ለመከላከል እርምጃ መውሰድ የጀመረችው አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳይኖር ነበር።
ድንበሮቿንም ወደ አገራቸው ከሚገቡ ዜጎቿ በስተቀር ለተጓዦች ዝግ ያደረገችው ቀድማ ነበር።
ከዚህም ባሻገር ወደ አገሪቷ የሚገባ ማንኛውም ግለሰብ መንግሥት ባዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት መቆየትና መመርመር ግድ ነው።
እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎችም ውጤት አሳይተው ከሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአገሪቷ አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልነበረም።
በዚህ በወቅት በሽታውን ለመቆጣጠር ባደረገችው ጥረት እንዲሁም በቫይረሱ ተይዞ ሁለት ወራትን በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ላሳለፈው ስኮትላንዳዊ አብራሪ ላደረገችው እንክብካቤም አድናቆት ተችሯታል።
ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በታዋቂው ዳ ናንግ ሪዞርት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የመገኘታቸው አሳዛኝ ዜና ተሰምቷል።
በዚህ ወቅትም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቷ ጎብኝዎች በከተማዋ ውስጥ ነበሩ ተብሏል።
መንግሥት ረቡዕ ዕለት በከተማዋ ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣሉ በፊትም ከተማዋን ለጎብኝዎች ዝግ አድርጎ ነበር።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዳ ናንግ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስተር ጉየን ዡዋን ፑክ "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በፍጥነትና በትጋት እርምጃ መውሰድ አለብን" በማለት በአገሪቷ ያሉ ግዛቶችና ከተሞችን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቃቸውን የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።














