በማላዊ በድጋሜ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ መሪው አሸነፉ

ላዛሩስ ቻክዌራ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የማላዊ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ላዛሩስ ቻክዌራ በአገሪቷ እንደገና በተካሄደው ፕሬዚንደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

ላዛሩስ ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው በዚህ ምርጫ 58.57 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ተፎካካሪያቸውን ፒተር ሙታሪካን ማሸነፋቸውን የምርጫ ቦርድ ቅዳሜ ዕለት አስታውቋል፡፡

ፒተር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በተካሄደው ምርጫ እንዳሸነፉ ተገልጾ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ ይህንን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፤ ተፎካካሪያቸው ላዛሩስም ምርጫው ፍትሃዊ እንዳልሆነ በመግለጽ ለፍርድ ቤት አቤት ብለው ነበር፡፡

ጉዳዩን ሲያይ ነበረው የአገሪቷ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤትም ፒተር ያሸነፉት "በድምጽ ማጭበርበር" እንደሆነ በመግለጽ ያሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ውጤቱ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ማላዊ በኬንያ ከሦስት ዓመታት በፊት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተሰረዘባት ሁለተኛዋ አፍሪካዊ አገር ናት፡፡

ቅዳሜ ዕለት የዚህ ምርጫ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ላዛሩስ፤ "ድሌ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ነው" ሲሉ በማሸነፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

ደጋፊዎቻቸውም በመዲናዋ ሊሎንግዌ አደባባይ በመውጣት ርችት በመተኮስና የመኪና ጡሩምባ በማሰማት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ላዛሩስ ዛሬ ቃለ መሃላ ፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡