ሰሜን ኮርያዊው እንዴት በደቡብ ኮርያ የፓርላማ ወንበር አገኙ?

ታይ ዮንግ-ሆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታይ ዮንግ-ሆ
ታትሟል

ታይ ዮንግ-ሆ በደቡብ ኮርያ የፓርላማ መቀመጫ ያገኙ የመጀመሪያው ሰሜን ኮርያዊ ሆነዋል።

ግለሰቡ በአንድ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም የሰሜን ኮርያ ምክትል አምባሳደር ነበሩ። እአአ 2016 ላይ ከመላ ቤተሰባቸው ሰሜን ኮርያን ካዱ። ይህም ሰሜን ኮርያን የካዱ ትልቁ ባለስልጣን አድረጓቸዋል።

በደቡብ ኮርያ መዲና ሶል 'ዩናይትድ ፊውቸር ፓርቲ' የተባለ የተቃዋሚ ፓርቲ ዋና እጩ ሆነው ትናንት በተካሄደው ምርጫ ተሳትፈዋል።

ከዚያም 58.4 በመቶ የሆነ ደምጽ በማግኘት ማሸነፍ ችለዋል። የድላቸው ዜና ሲሰማም ታይ ዮንግ-ሆ በደስታ ሲያነቡ ታይተዋል።

ታይ ዮንግ-ሆ የእርሳቸው ድል በትውልድ አገራቸው ሰሜን ኮርያ ለሚገኙ ቁንጮ የመንግሥት ባለስልጣናት የእርሳቸውን አይነት እርምጃ ቢወስዱ በአምባገነኑ ኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ላይ የሚያስከትሉትን ክስረት ያሳያል ብለዋል።

"ልነግራቸው የምፈልገው የወደፊት እጣቸው ብሩህ ሊሆን እንደሚችል ነው" ብለዋል።

ደቡብ ኮርያ ትናንት ባካሄደችው ምርጫ ገዚው ፓርቲ ከአጠቃላይ 300 መቀመጫ 163 ያክልን በመያዝ አጠቃላይ ምርጫውን ማሸነፉ መዘገቡ ይታወሳል። በኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ወቅት በተካሄደው ምርጫ ሪከርድ በሆነ ቁጥር 66 በመቶ የሚሆኑት ደምጽ ሰጪዎች ለወኪሎቻቸው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

በሶል የምትገኘው የቢቢሲዋ ሎውራ ቢከር፤ ታይ ዮንግ-ሆ ወደ ደቡብ ኮረርያ ከተሻገሩ በኋላ ደምጻቸውን አጥፍተው ሰላማዊ ኑሮን መምራት ሲችሉ፤ ስማቸውን ተጠቅመው ሰሜን ኮርያውያን በአምባገነን አገዛዝ ሥር የሚከፍሉትን ፍዳ ከማጋለጥ አልቦዘኑም ትላለች።

ታይ ዮንግ-ሆ ከሰሜን ኮርያ ሸሽተው በደቡብ ኮርያ ተጠልለው የሚገኙ ከ33ሺህ በላይ የአገራቸው ሰዎችም በደቡብ ኮርያ የሚደርስባቸው ፈተና ገልጠው አሳይተዋል።

የእርሳቸው የፖለቲካ ድል ለበርካታ አርአያ እንደሚሆንም ላውራ ትናገራለች።

ታይ ዩንግ-ሆ በደቡብ ኮርያ ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ ለደቡብ ኮርያ ፓርላማ ኮሚቴ አባላት ሲናገሩ፤ ሰሜን ኮርያውያን ለባርነት በቀረበ መልኩ ሕይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ ብለዋል።

ታይ ዩንግ-ሆ ሰሜን ኮርያን መክዳታቸው ከተሰማ በኋላ የኪም ጆንግ ኡን የመንግሥት ሚስጥርን አባክነዋል ሲል ከሷቸዋል።

በየዓመቱ ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ሰሜን ኮርያውያን ከአገራቸው ሸሽተው ይወጣሉ።