ኮሮናቫይረስ፡ በወራቤ "ርቀታችሁን ጠብቁ" ያለው ወጣት ሕይወቱ አለፈ

ወራቤ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, ወራቤ ከተማ አተስዳደር

ታትሟል

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በተለምዶ ዋሽንግተን በሚባለው አካባቢ ከትናንት በስቲያ አንድ ግለሰብ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚመከሩት ጥንቃቄዎች መካከል አንዱ የሆነው ርቀት መጠበቅን መምከሩ ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት ሆኗል።

በአንድ ሻይ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ሟች አራት ደንበኞች ተጠጋግተው መቀመጣቸውን ተመልከቶ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ መንገሩን ተከትሎ በተፈጠረ ግብግብ ሕይወቱ ልታልፍ እንደቻለች የስልጤ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃለፊ የሆኑት አቶ ሙዲን ሙኒር ለቢቢሲ ገልፀዋል።

''የሚሰራበት ሻይ ቤት በር ላይ ሰዎች ሰብሰብ ብለው መቀመጣቸውን ሲያይ ለምን ተራርቃችሁ አትቀመጡም ብሎ ሀሳብ ያቀርባል። ሰዎቹም ሃሳቡን ካላመረዳት ሊሆን ይችላል፤ በመካከል በተፈጠረ ግብግብ ደብድበው ገድለውታል።''

አቶ ሙዲን አክለውም ''በቦክስ ነበር ድብደባውን የፈጸሙበት፤ ሕይወቱ በቦታው አላላፈችም ነበር። ፖሊስ በቦታው ከደረሰ በኋላ ሰዎች ተረባርበው ወደ ወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቢወስዱትም ሕይወቱን ግን ማትረፍ አልተቻለም'' ብለውናል።

የሟች ሬሳም በወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ለቤተሰቦቹ ተመልሶ የቀብር ስነስርአቱ ተፈጽሟል።

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የነገሩን ደግሞ የስልጤ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ካሚል ሀሚድ ናቸው።

''አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል። በአሁኑ ሰአት መረጃ የማጠናከር ስራ እያከናወንን ነው። ቃላቸውን ተቀብለን፤ ከዛ በኋላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አድርገናል። ለእኛ የሰጡንን ቃል ለፍርድ ቤት አረጋግጠዋል። አሁን ፍርድ ቤቱ የሰጠን ቀጠሮ እስኪደርስ እኛ ጋር ይቆያሉ።'' ብለዋል።

ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ በወራቤ ዞን ሰዎች ራሳቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁና የተላለፉ ውሳኔዎችን ከማስከበር አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው የሚል ጥያቄ ለኢንስፔክተር ካሚል አቅርበንላቸው ነበር።

እሳቸውም '' ተሽከርካሪዎች መጫን በሚፈቀድላቸው ልክ ተሳፋሪዎችን እንዲጭኑ እየተቆጣጠርን ነው። በቁጥጥር ስር ያዋልናቸውም ግለሰቦች አሉ፤ ነገር ግን እያስተማርን እየለቀቅናቸው ነው። በአሁኑ ሰአት ማህበረሰቡ በሽታውን በደንብ እንዲገነዘብ ማድረጉ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው'' ብለዋል።

አክለውም '' ግለሰቦችን ሰብስቦ ማሰሩ በራሱ ሌላ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል። በዋናነት በመግባባትና በማሳመን ሰዎች ከበሽታው ራሳቸውን እንዲጠብቁ እየሰራን ነው'' ብለዋል።

የዞኑ የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ሙዲን በበኩላቸው ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ኮሮና ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

''በአካባቢው ቋንቋ ስልጥኛና አማርኛን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ እያደረስን ነው። ሶስት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገናል፤ የቫይረሱ መተላለፊያ፣ መከላከያ እና ከተያዙ ደግሞ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ታች ድረስ ወርደን ለማስተማር እየሞከርን ነው።''

መጨባበጥና ተቀራርቦ መንቀሳቀስን በተመለከተ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እየተገበረው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙዲን እንደ ገበያና ወፍጮ ቤት የመሳሰሉ ቦታዎች ላይ ግን አሁንም ችግር አለ ብለዋል።

ለማህበረሰቡ ተጨማሪ ግንዛቤ ለመፍጠርም እንደነ መሀመድ ሲርጋጋና አሊ ኑርን ያሉ ታዋቂ የአካባቢው ተወላጆችን በመጠቀም መልእክቶች እየተላለፉ መሆኑንም አቶ ሙዲን ገልጸዋል።

ኮሮና
Banner