ኮሮናቫይረስ፡ በአህጉረ አፍሪካ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ ከ10 ሺህ ገደማ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እስካሁን ድረስ 52 የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንደሚገኙባቸው ታውቋል። የአፍሪካ ሕብረት በሽታ መቆጣጠርያና መከላከያ ማዕከል እንዳስታወቀው በአፍሪካ 9,457 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 442 ሰዎች ሲሞቱ 800 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

በሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ሶስት ሰዎች መያዛቸው ከታወቀ በኋላ፣ በአፍሪካ እስካሁን ድረስ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱን ያላስመዘገቡ አገራት ኮሞሮስ፣ ሌሴቶ ብቻ ሆነዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት እንዳሉት ከሆነ አፍሪካ የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት 100 ቢሊየን ዶላር ትፈልጋለች።

እኚህ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ከፍራንስ 24 ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ አፍሪካ በማህበራዊና በምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች በርካታ ጥረት ብታደርግም አሁንም ግን " አቅሟ ደካማ ነው" ብለዋል።

አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ በትናንትናው ዕለት ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ ሁለተኛ ዙር እርዳታው መላኩን አስታውቋል።

የአፍሪካ መንግሥታት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስዱም ከዕለት ዕለት ግን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በጋና 73 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር 287 አድርሶታል።

በደቡብ አፍሪካም በርካታ ሰዎች መንግሥት የጀመረውን ምርመራ ሲሸሹ ተስተውሏል።

ኮሮና
Banner

ይህም የሆነው መንግሥት ቫይረሱን ለመመርመር የሚጠቀምበት መሳሪያ ራሱ ተበክሏል የሚል ሐሰተኛ ዜና በመሰራጨቱ እንደሆን ተገልጿል።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ባለስልጣናት እንዲህ አይነት ሐሰተኛ ወሬዎች መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያደርገውን ጥረት ያኮላሻል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በአፍሪካ የኮሮናቫይረስን የመዋጋቱን ጥረት ሐሰተኛ ዜና ብቻ ሳይሆን ፍርሃትም እየገጎዳው እንደሆነ እየታየ ነው።

በኮትዲቯርም ቢሆን በትናንትናው ዕለት በምንኖርበት አካባቢ የኮቪድ-19 ምርመራ አይደረግም፤ ቫይረሱን ወደ ቀያችን ያመጣብናል ያሉ ነዋሪዎች መመርመሪያ ጣቢያውን አውድመዋል።

በማላዊ ሁለት ሞዛምቢካውያን ቫይረሱን እያሰራጩ ነው በሚል ሐሰተኛ ዜና ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ተዘግቧል።

ደቡብ አፍሪካ የኮቪድ-19 በተያዙ ሰዎች ቁጥር ብዛት በአፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን ካሜሮን ደግሞ 658 ሰዎችን በማስመዝገብ ትከተላታለች።