የዩናይትድ ኪንግደምና አፍሪቃ ጉባዔ፡ 'ብሬግዚት' ለአፍሪቃ የሚፈይደው ምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝ ከአውⶂጳ ሕብረት ጋር ፍቺ ለመፈፀም ከወሰነች በኋላ ዓይኗን ወደ አፍሪቃ ለማዞር የሻተች ትመስላለች። ዩኬ-አፍሪቃ የተሰኘው ጉባዔም በሎንዶን ይካሄዳል። ግን ጥያቄው አፍሪቃ ከዚህ ምን ታተርፋለች የሚለው ነው።
ንግድ የተወሳሳበ ነው፤ የንግድ ስምምነት ደግሞ የባሰ። ሃገራት በንግድ ጉዳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያደርጓቸው ውይይቶችም ቀላል ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም።
እንግሊዝ ከአውሮጳ ሕብረት ጋር የነበራትን ትብብር ሙሉ በሙሉ ካፈረሰች በኋላ ከሕብረቱ ጋር የሚያስማማትን የንግድ ስምምነት ማቅረብ አለባት። ይህ ካልሆነ ደግሞ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት ሕጎች ልታመራ ነው።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና የብሬግዚት ደጋፊዎች ከአውሮጳ ሕብረት ለመውጣት ቸኩለዋል። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የንግድ ስምምነቶችን በነፃነት ማካሄድ ነው።
የአፍሪቃ ትርፍ
የዩናይትድ ኪንግደም ዕድገት ሚኒስትር አሎክ ሻርማ የእንግሊዝና አፍሪቃን መፃዒ ዕጣ ፈንታ ሲያስቡ ፊታቸው ይበራል። ንግዱ፣ ገበያው እና መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱ ይጧጧፋል ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት ዩናይትድ ኪንግደም ከአፍሪቃ በሚደረግ የንግድ ስምምነት አትቀልድም።
ዩኬ-አፍሪቃ የመዋዕለ-ንዋይ ጉባዔ እንደ አንድ ምሳሌ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን መሬት ላይ የወረደ የንግድ ስምምነት ለማየት ጊዜው አሁን አይመስልም። ዓመታት ሊቆጠሩ ይችላሉ።
የእንግሊዝ ከሕብረቱ መውጣት ምን ይቀይራል?
እንግሊዝ በያዝነው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ከአውሮጳ ሕብረት ጋር ያላትን ፍቺ ትፈፅማለች ተብሎ ይጠበቃል። ቢሆንም የሕብረቱ ጉምሩክ እና ገበያ ማሕበር አባል ሆና ትቀጥላለች።
እንግሊዝ የዚህ ማሕበር አባል ሆና ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት መቆየት ብትሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይህን ሃሳብ የሚደግፉት አይመስሉም። ይህ ማለት በያዝነው ዓመት በእንግሊዝና አፍሪቃ መካከል ይህ ነው የሚባል የንግድ ግንኙነት አይኖርም። ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ አፍሪቃ ከዚህ በፊት ውል ስትፈፅም የነበረው ከአውሮጳ ሕብረት ጋር እንጂ ከእንግሊዝ ጋር አለመሆኑ ነው።
ከ2020 በኋላ ባለው ጊዜ ግን የአፍሪቃ ሃገራትና እንግሊዝ የየራሳቸውን ስምምነት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እንደሚደርሱ እሙን ነው። የአውሮጳ ሕብረትና የአፍሪቃ ሃገራት የንግድ ስምምነት ሲያደርጉ ቃል የገቧቸው ቅድመ-ስምምነቶች እንግሊዝ መንካት የምትፈልግ አትመስልም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩኬ ከ70 ሃገራት ጋር ከ40 በላይ የንግድ ስምምነቶች አድርጋለች።
አፍሪቃ ከዩኬ ትጠቀም ይሆን?
ከአውሮጳ ሕብረት የምትወጣው እንግሊዝ በፊት ካላት ያነሰ ጥንካሬ እንደሚኖራት ይጠበቃል። ይህ ማለት ከእንግሊዝ ጋር ውል የሚፈፅሙ የአፍሪቃ ሃገራት የተሻለ ጥቅም ያለው ስምምነት መፈረም ይችላሉ።
ነገር ግን ከላይ እንዳልነው የንግድ ስምምነቶች ውስብስብ ናቸው። ብልሃት ይጠይቃሉ። ጊዜና ገንዘብም ይሻሉ።
እንግሊዝ ከሕብረቱ እንደወጣች ማድረግ የምትሻው ነገር የንግድ ስምምነቶችን የሚፈፅሙ አካላትን ማጠናከር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝ ከአውሮጳ ሕብረት ትውጣ እንጂ የመጀመሪያና የመጨረሻ የንግድ አጋሯ ሕብረቱ ነው። ከዚያ በመቀጠል ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና አውስትራሊያ በንግዱ ዘርፍ ከአንግሊዝ ቀኝ የሚሰለፉ እንደሆኑ ጥርጥር የለም። በዚህ ረገድ የአፍሪቃ ዕጣ ከወደ ኋለኞቹ ነው የሚሆነው።
ነገር ግን ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉ አንዳንድ አፍሪቃ ሃገራት ከአውሮጳ ሕብረት ጋር ከባድ ንግድ ውስጥ ናቸው። ማዕድን፣ መኪናና የግብርና ውጤቶች ወደ አውሮጳ ገበያ ከሚተሙ የአፍሪቃ ምርቶች መካከል ናቸው። 18 በመቶውን የምትይዘው ደግሞ እንግሊዝ ናት።
እንግሊዝ ከአውሮጳ ሕብረት ፍቺ በኋላ ወደ ኢኮኖሚ ድቀት የምትገባ ከሆነ ግን ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉ ሃገራት በተዘዋዋሪ ሊመቱ ይችላሉ። ደቡብ አፍሪቃ የእንግሊዝ 8ኛ ከፍተኛ የንግድ አጋር ናት።
ኬንያ ደግሞ የአበባ ምርቶችን ወደ እንግሊዝ በመላክ የሚተካከላት አልተገኘም። ኬንያ ወደ አውሮጳ ከምትልከው አበባ 18 በመቶው መዳረሻው እንግሊዝ ነው። የእንግሊዝ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ውስጥ መግባት ለኬንያ የአበባ ገበያም አስጊ ሊሆን ይችላል። የኬንያ የአበባ ዘርፍ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን አቅፏል።
የቀረጥ ጉዳይ አሁንም ማነጋገሩን እንደቀጠለ ነው። ወደ አውሮጳ ገበያ የሚላኩ የአፍሪቃ ምርቶች በቀረጥ ይጎዳሉ። ቀረጡ የሚቀነስ ከሆነ የአፍሪቃ ሃገራት መጠቀማቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
የአፍሪቃ ሃገራት ከእንግሊዝ ጋር ለመምከር በዩኬ - አፍሪቃ የንግድ ጉባዔ ላይ ተገናኝተው የሚመክሩት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ይሆናል።













