ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውስትራሊያ ተፈጥሯዊ ፈተና ከሰደድ እሳት ወደ አውሎ ንፋስ ሊቀየር ነውን?
አውስትራሊያ ወራትን ባስቆጠረ የሰደድ እሳት ስትለበለብ ከርማለች። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳትን ያጠፋውንና ከአስር ሚሊዮን በላይ ሄክታር ያጠፋውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ሰሞኑን የሚጥለው ዝናብ በብዙ አውስታራሊያዊያን ልብ ዘንድ ደስታንና ተስፋን ፈንጥቋል።
ይህ ደስታቸውና ተስፋቸው ግን ከቀናት በኋላ ጨልሟል። አውስትራሊያ ተፈጥሯዊ ፈተናዋ ከእሳት ወደ ውሃ እየተቀየረ ነው ተብሏል። አውሎ ንፋስ።
ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት የአውስትራሊያዋ ቪክቶሪያ ግዛት አዝናነብ በቀላቀለ ከፍተኛ የአውሎ ንፋስ ልትመታ ትችላለች።
በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በግዛቷ ሰፊ ውድመት እያደረሰ ያለውን የሰደድ እሳት ድራሹን አጥፍቶታል። ይህ እፎይ የሚያስብል ተፈጥሯዊ ምላሽ ሆኖ ለወራት የቀጠለውን ውድመትና ሞት ገትቷል። ነገር ግን ከባድ ዝናቡ የፈጠረው መጠነ ሰፊ ጎርፍ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ቆራርጧል፣ መንገዶችን ዘጋግቷል።
በመስከረም ወር የጀመረው ሰደድ እሳት 28 ሰዎችን ሲገድል በሺዎች የሚቆተሩ ቤቶችን አውድሞ በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር ጥቅጥቅ ጫካን ደግሞ ዶጋ አመድ አድርጓል።
አሁን የተፈጠረው ርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ሰደድ እሳቱን ማብረድ ሲጀምር መንግስት ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ድጎማ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስኮት ሞሪሰን እንዳሉት ዘርፉን ለማበረታታት 76 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ይመደባል። በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የቢዝነስና የቱሪዝም ዘርፎች ድጎማው ይደረጋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ "ይህ በህይወት እያለን የምናስታውሰው የገጠመን ትልቁ ተግዳሮት ነው" ብለዋል።
የአውስትራሊያ የቱሪዝም ም/ቤት ለሮይተርስ እንደተናገረው ሰደድ እሳቱ 1 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር የሚጠጋ ኃብት አውድሟል። የአውስትራሊያው የቱሪዝም ኤክስፖርት ም/ቤት ደግሞ ውድመቱ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 4.5 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ይደርሳል ብሏል።
በአውስትራሊያ ላይ የተደቀነው ተፈጥሯዊ ፈተና ግን አሁንም የቆመ አይመስልም። የአገሪቱ የሜትሪዎሎጅ ቢሮ እንዳስታወቀው ከሆነ አሁን በተለይ በቪክቶሪያ ግዛት ሊደርስ የሚችለው ውድመት በሰደድ እሳት ሳይሆን ሰደድ እሳቱን ያበርዳል ተብሎ ተስፋ በተደረገበት ዝናብ አማካኝነት ነው። ከፍተኛ የአውሎ ንፋስ የግዛቷን ሰፊ አካባቢ ያጥለቀልቃል የሚል ትንበያ ከቢሮው ተሰምቷል።
ይህ አውሎ ንፋስና ከባድ ዝናብም ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የቪክቶሪያ ግዛትን ይንጣታል ብሏል የቢሮው የማስጠንቀቂያ ትንበያ።
በግዛቷ ከፍተኛው ዝናብ እየጣለ ቢሆንም እስካሁን ቢያንስ በ14 አካባቢዎች ሰደድ እሳቱ ማውደሙን እንደቀጠለ ነው።
በተለያዩ ግዛቶችም በተመሳሳይ አሁንም ሰደድ እሳቱ እንዳለ የሚናገሩት የአገሪቱ ባለስልጣናት ነገር ግን ድንገተኛው ከባድ ዝናብና አውሎ ንፋስ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ በተለይ በባሕር ዳርቻዎች አካባቢ በጎርፍ የመጥለቅለቅና የሃይቆች ማዕበል የተለያዩ ቅሪቶችን ሊተፋ ስለሚችል ዜጎች ቆይታቸውን በከፍተኛ ቦታዎች እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።