በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች በረኃብ ሞቱ

በዚምባብዌ ያሉ ዝሆኖች

የፎቶው ባለመብት, MARTIN BUREAU

ታትሟል

በዚምባብዌ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ቢያንስ ሁለት መቶ ዝሆኖች መሞታቸውን ባለስልጣናቱ አሳውቀዋል።

ዝሆኖቹ የሞቱት ምግብና ውሃ በማጣታቸው መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው ባለፈው ወርም 55 ዝሆኖች መሞታቸው ተገልጿል ።

የሟች ዝሆኖች ቁጥር ከዚህ በላይም እንዳያሻቅብም 600 የሚሆኑ ዝሆኖች ወደ ደቡባዊ ምስራቅ ክፍል ወደሚገኙ ሶስት ፓርኮች የማዛወር ስራም እየተሰራ እንደሆነ የዚምባብዌ ፓርክ ባለስልጣን ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩም አክለው ዝናብ እስካልመጣና ድርቁን መከላከል ካልተቻለ ለበርካታ ዝሆኖች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ይሆናል ብለዋል።

በኃገሪቷ ታሪክ ውስጥ እንስሳትን በከፍተኛ ሁኔታ ማዛወር በተባለው በዚህ ሂደት ከዝሆኖች በተጨማሪ ቀጭኔዎች፣ አንበሶች፣ ጎሽ እንዲሁም ሌሎች እንስሶችም ወደሌላ ፓርኮች ይወሰዳሉ ተብሏል።

በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ዝሆኖች ውስጥ 80 ሺ ዝሆኖች የሚሆኑት በዚምባብዌ የሚገኙ ሲሆን ይህም አምስተኛ ደረጃን እንድታገኝ አስችሏታል።

የፓርኩ ኃላፊዎች እንደሚናገሩት ዝሆኖቹን በአካባቢውም ማቆየት ስላልቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖችም ወደ ቻይና ተዛውረዋል።

የእንስሳት ደህንነት ተሟጋች ቡድኖችም ይህንን ተችተው አውግዘውታል።