አምስተርዳም ውስጥ በስህተት የአደጋ ምልክት የተጫነው አብራሪ ሽብር ፈጠረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በስህተት 'አውሮፕላኑ ተጠልፏል' የሚለውን የአደጋ ጊዜ ጥሪ የተጫነው አብራሪ በአምስተርዳሙ የስኪፖል አውሮፕላን ማረፊያ ሽብር ፈጥሯል።
የኔዘርላንድስ ፖሊስ ረቡዕ ማታ 3፡30 ገደማ አንድ አጠራጣሪ ጉዳይ ስለገጠማቸው አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን በትዊተር ገፃቸው አሳውቀው ነበር።
በአውሮፓ እጅግ ሥራ ብዙ ከሆኑ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ የሆነው ስኪፖል የተወሰነ ክፍል ተዘግቶ ፖሊስ ምርመራ ማካሄድ ጀምሮ ነበር።
ከአንድ ሰዓት በኋላ ግን አንድ አውሮፕላን አብራሪ በስህተት የተጠልፊያለሁ ቁልፍን በመጫኑ ነው ሁከት የተፈጠረው ሲል ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ከአምስተርዳም ወደ ስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ሊበር እየተዘጋጀ የነበረው አውሮፕላን አብራሪ የተጫነው ቁልፍ ጠላፊዎች አውሮፕላን ውስጥ ገብተዋል የሚል ምልክት የሚሰጥ ነው።
ፖሊስ ሁሉንም ተሣፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞች ከአውሮፕላኑ በጥንቃቄ ካስወጣ በኋላ ሁሉም ሰላም መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ፎቶዎች መንገደኞች ጥግ ጥግ ይዘው መረጃ ሲጠባበቁ ያሳያሉ። ቢሆንም በሌላው የአውሮፕላን ማረፊያው ክፍል መደበኛ ሥራ እየተከወነ ነበር። በአደጋ ጊዜ ጥሪው ምክንያት ለጊዜው በረራቸው የተስተጓጎለ መንገደኞችም ነበሩ።
ግርገሩ መሃል የነበረው የ38 ዓመቱ ሮቤርቶ ካሬራ «ፓይለቱ የሆነ ነገር እንዳጋጠመው ጠቆመን» ሲል የተፈጠረውን ለቢቢሲ በስልክ አስረድቷል። ከዚያም አንድ ጥግ ላይ ተወስደው ሁኔታው እኪረጋጋ ድረስ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል እንደቆዩ ይናገራል።
ምንም እንኳ የሆነ ነገር እንደተፈጠረ እና ፖሊስ እያጣራ እንዳለ በግልፅ ቢታይም ሁኔታዎች የተረጋጉ ነበሩ ተብሏል።












