በደምበጫው የመኪና አደጋ የሞቱት ቁጥር 23 ደረሰ

ታትሟል

በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን በደምበጫ ወረዳ ትናንት በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ 16 የነበረው የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ፖሊስ ገለጸ።

በደረሰው የመኪና አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሰባት ጨምሮ 23 መድረሱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ባለሙያ የሆኑት ምክትል ኮማንደር መሠረት ላቀ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ 6 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ የትራፊክ አደጋ 17 ወንዶችና 6 ሴቶች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን በሕዝብ ማመላለሻ ውስጥ የነበሩት ተሳፋሪዎች የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን ምክትል ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ትናንት መስከረም 12/2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አንድ የጭነት ማመላለሻ አይሱዙ ከሁለት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችንና አንድ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በመግጨቱ አደጋው መድረሱን ምክትል ኮማንደሩ አስታውሰው እስካሁን ድረስ አንድ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ልንገርህ ይታይህ የደምበጫ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው ትናንት በወረዳቸው ከቀኑ 6፡30 አካባቢ አደጋው መድረሱን ጠቅሰው ከደምበጫ ከተማ ወደ ፍኖተ ሰላም በሚወስደው ቁልቁለታማና ጠመዝማዛ መንገድ ላይ ልዩ ስሙ ድፍር በሚባል አካባቢ ግጭቱ መከሰቱን ተናግረዋል።

አደጋውን ያደረሰው አይሱዚ ከፍኖተ ሰላም አቅጣጫ ወደ ደምበጫ በቆሎ ጭኖ እየመጣ የነበረ ሲሆን፣ ሁለት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች እና አንድ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ደግሞ ከደምበጫ ከተማ ተነስተው ወደ ፍኖተ ሰላም አቅጣጫ የሚጓዙ እንደነበሩ ይናገራሉ።

መኪኖቹ በጠመዝማዛው መንገድ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ተከታትለው ይጓዙ እንደነበር የገለጹት አቶ ልንገርህ በአንደኛው ሚኒባስ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪው ሙሉ በሙሉ መሞታቸውን ገልፀዋል።

21ዱ የጉዳቱ ሰለባዎች ሕይወታቸው ያለፈው እዚያው አደጋው የደረሰበት ስፍራ ምንም ዓይነት እርዳታ ሳያገኙ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው መኪኖቹ ፊት ለፊት ስለተጋጩ ተጣብቀው ስለነበር እነርሱን ማላቀቅ በርካታ ሰዓት መውሰዱን ይናገራሉ።

አስክሬኖችን ክፉኛ ከተጋጨው መኪና ውስጥ ለማውጣት ፖሊስና ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የተናገሩት ኃላፊው በአደጋው ወዲያው ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 15 ወንዶችና 6 ሴቶች በአደጋው ስፍራ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ለሕክምና ከተላኩ በኋላ ከመካከላቸው አንድ ሴትና አንድ ወንድ ሞተው አስከሬናቸው ወደ ደምበጫ መምጣቱ አረጋግጠዋል።

የሟቾቹ አስክሬን ማንነት የመለየት ሥራ ፈታኝ እንደነበር የሚያስታውሱት ኃላፊው በመታወቂያቸውና በሚያውቋቸው ሰዎች እንዲለዩ ከተደረገ በኋላ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ሁሉም አስክሬኖች ወደ አካባቢያቸው መሸኘታቸውንና ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን ተናግረዋል።

በህዝብ ትራንስፖርት ሲጓዙ ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች በተጨማሪ የደረቅ ጭነት መኪናውና የአንደኛው ሚኒባስ አሽከርካሪዎችም በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉን አቶ ልንገርህ ገልጸው፤ ሌላኛው የሚኒባስ ሹፌር የአካል ጉዳት ደርሶበት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል ሲላክ የባለ ሦስት እግሩ አሽከርካሪ ግን ቀላል ጉዳት ስለደረሰበት ሕክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ መመመለሱን ተናግረዋል።

በወረዳቸው ስድስት አምቡላንስ መኖሩን ያስታውሱት አቶ ልንገርህ አራቱ ለጥገና ወደ ጋራዥ በመግባታቸው አደጋው ባጋጠመበት ወቅት ሁለት አምቡላንሶች ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ቦታ ለመውሰድ የነበሩት አምቡላንሶች ከስፍራው በቶሎ ቢደርሱም መኪኖቹ በከባድ ሁኔታ ተጋጭተው በመጣበቃቸው ተጎጂዎቹን ከሚኪኖቹ ለይቶ ለማውጣት ረጅም ጊዜ ወስዶ እንደነበር ተናግረዋል።