የእናቶች ቀን፡ እናቶች ምን ይላሉ?

እናትና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዓለም ዙሪያ በዓመት ውስጥ 31 የተለያዩ ቀናት እናቶችን ለማክበርና ለመዘከር ተመድበዋል። የተለያዩ ሃገራት በተለያየ ቀን ላይ የእናቶችን ሚና እና ማንነት ሲያከብሩና ሲያስቡም ይውላሉ።

በዛሬው ዕለት አሜሪካ፣ ፊሊፒንስ፣ ቬኔዝዌላ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛንያ፣ ኢትዮጵያ እና ከ80 በላይ ሌሎች ሃገራት የእናቶችን ቀን ያከብራሉ። ለእናቶቻቸው አበባ በመግዛት፣ ምሳ በመጋበዝም ሆነ ቁርስ ሠርቶ ጠዋት እናቶቻቸውን በማሳረፍ ቀኑን የጀመሩት አሉ።

የወይንሐረግ አሸናፊ የሦስት ልጆች እናትና ከሁለት ሴት ልጆቿ የልጅ ልጅ ያዩ ሲሆን "ዛሬ የእናቶች ቀን ነው እስክትሉኝ ድረስ በአዕምሮዬም አልመጣልኝም ነበር። ከቤተ-ክርስትያን መጥቼ ምሳ ለመሥራት እየተሯሯጥኩ ነው" ይላሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ብዙ እናቶች የእናትነት፣ የባለቤትነታቸውንና የሠራተኛ ግዴታቸውን በመወጣት ቀኖቻቸው የተወጠሩ ናቸው። ልክ እንደ የወይንሐረግ ዕለቱ የእናቶች ቀን መሆኑን የዘነጉም ብዙ ናቸው።

ምሥራቅ ነፃነት "ጠዋት አንዳንድ ጉዳዮችን ለመጨረስ በወጣሁ ገዜ ራድዮ ላይ ሰምቼ ነው እንጂ፤ ዛሬ መሆኑ ምንም ትዝ አላለኝም" ብላለች። እንደሰማችም እናቷ ጋር ደውላ ያላትን ፍቅርና አክብሮት እንደገለፀችላትም አጫውታናለች።

ምሥራቅ ለእናቷ አበባ ገዝታ ብትሰጣትም የእርሷ ልጆች ቀኑን አስመልክተው ምን እንዳደረጉላት ስንጠይቃት "በእኛ ሃገር ብዙ ስላልተለመደ ይመስለኛል እነርሱ ምንም አላደረጉልኝም። እንደውም አሁን የእነርሱን ፕሮግራም ... ልደት ምናምን ለማሳካት እየተሯሯጥኩ ነው" ብላለች።

ቀኑን አስታውሳም እንደወትሮው ቀኑን ማክበር አልቻልንም የምትለን ነባት አባስ በረመዳን ፆም ላይ ስለሆኑ "እንደሌላ ጊዜው አብረን ቁርስ ማድረስ አልቻልንም። ማታ ግን ለኢፍጣር ደስ የሚል ነገር እንደምናደርግ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።

እናትና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አክላም አዲስ አበባ የአበባው ሽያጭ መጧጧፉን ገልፃ "በአሁኑ ዓመት ከሌላው ጊዜ በተለየ ከተማዋ የእናቶችን ቀን እያከበረች ትመስላለች። እንደውም በማህበራዊ ገፆቻቸው ላይ ሰዎች ከስማቸውና ከአባታቸው ስም መካከል የእናታቸውን ስም በማካተት ፌስቡክን አጥለቅልቀውታል። እኔም ነባት ነጃት አባስ እሆናለሁ ማለት ነው" ትላለች ሳቅ እያለች።

"እናቴ ምን ያህል መስዋትነት እንደከፈለች የታወቀኝ እኔም እናት ስሆን ነበር። የዛሬው ዕለት ለወለዱ እናቶች ብቻ ሳይሆን የእናትነት ግዴታውን፣ ፍቅሩን፣ እንክብካቤውን እንደ እናት አንዳንዴ ደግሞ ከእናትም በላይ ለሚሆኑትም እናቶች፣ አያቶች፣ አክስቶችና እህቶችም ማሰቢያ መሆን አለበት" ትላለች ነባት።

ወ/ሮ አዜብ መርሻ በሌላ ጊዜ የእናቶችን ቀን ለየት ባለ መልኩ የምታከብር ቢሆንም በሕመም ምክንያት የልጆቿን አባት በሞት ያጡት ከቀናት በፊት በመሆኑ መላው ቤተሰብ ጥልቅ ሃዘን ላይ መሆናቸውን ግልፃልናለች።

ልጆቹም ሕፃናት በመሆናቸው የአባታቸውን በሞት መለየት የእናትነት ግዴታዋን ከመወጣትም ባሻገር እንዴት አድርጋ እንደምታስረዳና በዚህ በሃዘን ወቅት ልጆቿን እንዴት እንደምትረዳ ግራ መጋባቷን ነግራናለች።

ስቴፋኒያ ቲሬላ ክልስ ኢትዮጵያዊት ስትሆን ሁለት ልጆቿን በአዲስ አበባ እያሳደገች ትገኛለች። "እረፍት በጣም ስለሚያስፈልገኝ ዛሬ ቤቴ ቁጭ ብዬ ምንም ነገር ሳላደርግ መዋል ነው የምፍለገው" ብላናለች።

እናቷን ያጣችው የመጀመሪያ ልጇን እንደወለደች ስለነበር ምን ጊዜም እናቷን ብታስባትም የእናቶች ቀን በሚመጣበት ጊዜ ግን ማሰብም እንደማትፈልግ አጫውታናለች።

ምሥራቅ ደግሞ በቅርቡ ከቅጥር ሥራ ወደ ግል ንግድ የተሰማራች ሲሆን "እንደ ድሮ 2 ሰዓት ገብቼ 11 ሰዓት ስለማልወጣ ከልጆቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ለባለቤቴም የምሰጠው ጊዜ በጣም ተቀይሮብኛል።

ሥራንና እናትነትን በአንድ ላይ ባላንስ ጠብቆ መኖር ከባድ ነው ቢሆንም ግን እናት መሆኔን በጣም ነው የምወደው" በማለት ለልጆቿ ያላት ፍቅር ጥልቅ መሆኑን ነግራናለች።

አሁን ጡረታ ላይ ያሉት የወይንሐረግ "እናትነት ማለት ሃገር መሆን ነው፤ ምክንያቱም ሃገር ሁሉን ነገር እንደምትችለው ሁሉ እናትም ሁሉን ነገር ትችላለች" በማለት ቃላቶች እያጠሯቸው እንደሆነ እየተናገሩ ስሜታቸውን ገልፀዋል።

"ልጆቼን ሥራ እየሠራሁና ትምህርት እየተማርኩ ነው ያሳደኳቸው። ቀላል አይደለም እናት መሆን" ብለው "ያኔ የተቋቋምነው ወጣት ስለነበርን ነው አሁን በማረፊያዬ ደግሞ እስከ ልጅ ልጅ በማየቴ ደስታዬ ወደር የለውም" ብለውናል።

ብዙዎች ለእናታቸው ያላቸውን ፍቅር በተለያየ መልኩ ይገልፃሉ እናንተስ?