የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖችና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ የአንጫወትም ማስፈራሪያዎች

ታትሟል

ከጨዋታዎች በኋላ ከሚሰጥ የክፍያ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አንጫወትም እያሉ ሲያስፈራሩ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል።

በ32ኛው አፍሪካ ዋንጫም የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከምድባቸው ማለፋቸው ካረጋገጡ በኋላ የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሽልማት ክፍያውን ከፍ የማያደርግ ከሆነ እንደማይጫወቱ አስታውቀው ነበር።

ተጫዋቾቹ ስልጠናም አንሰራም በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የሀገሪቱ እግር ኳስ ማህበርም ልምምዳችሁን ቀጥሉ እኛ ገንዘቡን እንጨምራለን በማለት መደራደር መጀመሩ ይታወሳል። በመጨረሻም ከምድባቸው በማለፋቸው ብቻ ለእያንዳንዱ ተጫዋች 6000 ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል።

ይህ አጋጣሚ በዚህኛው አፍሪካ ዋንጫ ብቻ አራተኛው ክስተት ነው። የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አባላት ቃል የተገባልን 10 ሺ ዶላር ካልተሰጠን ወደ ስልጠና አንሄድም ብለው ነበር።

በተመሳሳይ የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን አባላት ከእግር ኳስ ማህበሩ ጋር በተፈጠረ ገንዘብ ነክ አለመግባባት ለውድድሩ ወደ ግብጽ ያቀኑት አርፍደው ነበር።

የዚምባብዌ ተጫዋቾችም ውድድሩን አቋርጠን እንመለሳለን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የአፍሪካ ብራዊ ቡድኖች አመፅ ምክንያት

ብሔራዊ ብድኖች ወደ ቀጣዮቹ ዙሮች ባለፉ ቁጥር የሚሰጣቸው የክፍያ መጠን ከፍ እያለ ይሄዳል። ይህ ማለት ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ በሚያገኘው ስኬት ላይ ተመስርቶ የሃገራቱ የእግር ኳስ ማሕበራት ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኛሉ።

በዚህ ምክንያት በውድድሩ በመሳተፋቸው ብቻ ተጫዋቾቹ ተጨማሪ ክፍያ ማግኘት ያለባቸው ሲሆን ወደ ቀጣይ ዙሮች ሲያልፉ ደግሞ ተጨማሪ ማበረታቻዎች ማግኘት አለባቸው።

በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ምናልባት የማበረታቻው ገንዘብ ክለቦቻቸው ሚከፍሏቸው ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በየሃገራቱ ሊጎች ለሚጫወቱት ተጫዋቾች ብዙ ትርጉም አለው።

ለምሳሌ ሁሉም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫው ለዕሩብ ፍጻሜ በመድረሳቸው ያገኙትን የማበረታቻ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለግሰዋል።

በአፍሪካ ሊጎች ለሚጫወቱትና በተለያዩ ውድድሮች ሃገራቸውን ወክለው የሚሄዱት ተጨዋቾች ግን ይህንን የማድረግ እድሉም የላቸውም። እንደውም ከሃገራቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማግኘት የሚገባቸው የማበረታቻ ገንዘብ ሲዘገይ አንዳንዴም ከነጭራሹ ሳይሰጣቸው ሲቀር ይስተዋላል።

ይህ ደግሞ ተጫዋቾቹን ወደ አመጽና ውድድሩን አቋርጠን እንመለሳለን ወደሚሉ ውሳኔዎች ይገፏቸዋል።

ተጫዋቾች አንጫወትም ባሉ ቁጥር ለሃገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን መጥፎ ስም ከማሰጠቱ ባለፈ ያለአግባብ ለግለሰቦች ጥቅም የሚውለው ገንዘብ ትኩረት ያገኛል፤ ከብክነትም ይድናል።

እንደ ዲዲየር ድሮግባ እና ጆርጅ ዊሃ ያሉ ትልልቅ ተጫዋቾች በሃገራቸው ሊግ ለሚጫወቱ የብሄራዊ ቡድን አባላት ድጋፍ በማድረግ ፌደሬሽኖች ላይ ጫና እስከማሳደርም ደርሰው ነበር።