ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጦር ወንጀል ፈጽሟል የተባለው ሩሲያዊ ወታደር የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት
ሩሲያ ወረራ ከጀመረች በኋላ በዩክሬን በተካሄው የጦር ወንጀል ችሎት ሩሲያዊ ሲቪል ሰው የገደለው ሩሲያዊው ታንከኛ ላይ የእድሜ ልክ እስራት በይኗል።
ከወራት በፊት ቫዲም ሺሺማሪም የተባለው ወታደር የ62 ዓመቱን ዩክሬናዊ ግለስብ በመግደል ጥፋተኛ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ወንጀሉን መፈጸሙን ያመነው ወታደሩ ይህንን እርምጃ የወሰደው በተሰጠው ትዕዛዝ መሆኑን ገልጾ የሟችን ባለቤት ይቅርታ ጠይቋል።
ዩክሬን የጦር ወንጀል እንደፈጸሙ የተጠረጠሩ በርካታ ወታደሮች ላይ ምርመራ እያካሄድች ሲሆን አብዛኞቹ ሆን ብለው ሲቪል ሰዎችን ከመግደል ጋር የተያያዘ ጉዳይ ያላቸው ናቸው።
ዩክሬን ከ11 ሺህ የሚልቁ የጦር ወንጀሎች ተፈጽሟል ስትል ትከሳለች። ሆኖም ማስረጃ ባታቀርብም ሩሲያ ይህንን ክስ የምታጣጥል ሲሆን ወታደሮቿ ሲቪል ሰዎችን ኢላማ አደርገው እንደማያውቁ ደጋግማ አሳውቃለች።
ይሁን እንጂ ሩሲያ በደፈናው ከምታጣጥለው ክስ በተቃራኒ የታንከኛውን ወታደር ጨምሮ በርካታ የጦር ወንጀሎችን እየመረመረች ትገኛለች።
ይህ የዩክሬን የጦር ችሎት ብይን የሩሲያን ወረራ ባይቀለብሰውም በታንከኛው ለተገደለው ሺፕሎቭ ባለቤት አይነት ሰዎች ፍትህን እያመጣ ነው።
ችሎቱን የመሩት ዳኛ የ21 ዓመቱ የሩሲያ ታንከኛ "የወንጀል ትዕዛዝን" አስፈጽሟል ብለዋል።
"የተፈጸመው ወንጀል በሰላም፥ ደህንነት፥ ሰብአዊነት እና ዓለም አቀፍ ህጋገት ላይ የተፈጸመ ነው። ፍርድ ቤቱ ከእድሜ ልክ እስራት የተሻለ አማራጭ አላገኘም" ሲሉ ገልጸዋል።
የተከሳሹ ጠበቃ ወሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተናግሯል።
በሩሲያ በኩል የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ያለቻቸውን ዩክሬናውያን የምትቀጣበት አዲስ ህግ እያዘጋጀች ትገኛለች።
ሺሺማሪም በሩሲያ የታንከኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ሲሰራ የቆየ ነው።
ወንጀሉን እንዲጸፈፅም ትዕዛዝ እንደደረሰውም ተናግሯል።
ጠበቃው ሺሺማሪም ሰውዬውን ላለመግደል ሁለት ጊዜ ትዕዛዙን አልቀበለም ማለቱን አስረድቷል። ሆኖም ለራሱ በመፍራቱ ለመተኮስ መገደዱን ገልጿል።
በችሎቱ ወስጥ የሞች ባለቤት ካትሪያና ሺልፖቫ "እባክህ ነገረኝ እዚህ ለምን መጣችሁ? እኛን ለመጠበቅ ነው ወይ?" እያሉ ተካሳሹን ሲሞግቱ ታይተዋል።
ግለሰቧ የፑቲንን ውሳኔ ትክክለኝነት ደጋግመው የጠየቁ ሲሆን "ከማነው የምትጠብቁን? ከገደልከው ባለቤቴ ነበር ስትጠብቁኝ የነበረው?" ሲሉ ለሰነዘሯቸው ጥያቄዎች የ21 ዓመቱ ወታደር ምላሸ አልነበረውም።
ሆኖም ያሉበት ሁኔታ ይገባኛል በማለት ይቅርታቸውን ጠይቋል።
ሺልፖቫ "ለልጁ በጣም አዝኛለሁ ግን ለእንዲህ አይነት ወንጀል ይቀርታ ላደርግ አልችልም" ብለዋል።
እንደተመድ ገለጻ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ባሃላ 3 ሺህ 835 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና 4 ሺህ 351 ተጎድተዋል።