ሕንዳውያኑ ወላጆች የልጅ ልጅ አላሳየንም ያሉትን ልጃቸውን ለምን ከሰሱ?

የህንጻ ልጅ ጫማ የያዙ የጥንዶች እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕንዳውያኑ ጥንዶች በ6 ዓመታት የትዳር ቆይታ የልጅ ልጅ ያላሳያቸውን ብቸኛ ልጃቸውና ሚስቱን ከሰዋል።
ታትሟል

ሰሞኑን በሕንድ ወደ ፍርድ ቤት ያመራው ያልተለመደ ክስ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ጥንዶቹ ብቸኛ ልጃቸውን እና ሚስቱን ከስድስት ዓመት የጋብቻ ቆይታ በኋላ የልጅ ልጅ አላሳዩንም ሲሉ ፍርድ ቤት ገትረዋቸዋል።

የ61 ዓመቱ ሳንጂቭ እና የ57 ዓመቷ ሳደሃና ፕራሳድ እንደሚሉት ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ፣ ለአብራሪነት ሙያ ሥልጠናው፣ ድል ላለ ሠርጉ ለመደገስ እና ለጫጉላው ሽርሽር ያጠራቀሙትን ገንዘብ አውለዋል።

አሁን ላይ ልጃቸው ይህንን ውለታ የሚመልስበት ጊዜ እንደሆነ ያስባሉ።

በመሆኑም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ልጃቸውና ሚስቱ የልጅ ልጅ እንዲያሳይዋቸው አሊያም 50 ሚሊዮን ሩፒ ወይም 650 ሺህ ዶላር እንዲከፍሏቸው ጠይቀዋል።

ወጣቶቹ ጥንዶች እስካሁን በዚህ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም። ይሁን እንጂ በወላጆቹ እና በልጃቸው መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት መሆኑን የፍርድ ቤት ክሱ ያመለክታል።

ሳድሃና ፕራሳድ፣ ልጃቸው እና ሚስቱ ልጆች እንዲኖራቸው ባለመፈለጋቸው ምክንያት በማኅበረሰቡ መሣቂያ እና መሳለቂያ እንደሆኑ ይህም በሥነ ልቦናቸው ላይ የተፈጸመ የጭካኔ ድርጊት እንደሆነ ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግረዋል።

"ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረንም። ልናነጋግራቸው ሞክረናል፤ ነገር ግን ስለልጅ ልጆች ባነሳን ቁጥር ደስ አይላቸውም። ልጅ ለመውለድ ያለመፈለጋቸው የቤተሰባችንን የዘር ሐረግ ማብቂያ ሊሆን ይችላል" ብለዋል እናት ሳድሃና።

ባለቤታቸው ሳንጂቭ በበኩላቸው "ደስተኞች አይደለንም። ጡረታ ወጥተናል። አያት መሆን እንፈልጋለን። የልጅ ልጆቻችንን ለመንከባከብና ለመጠበቅም ፈቃደኞች ነን። በሰዎች ሕይወት ውስጥ የልጅ ልጆች ደስታን ያመጣሉ። እኛ ግን ይህንን ተነፍገናል" ብለዋል።

እኚህ በልጃቸው ውሳኔ የተበሳጩት ወላጆች ታዲያ የልጅ ልጅ አላሳየንም ሲሉ በልጃቸው ላይ ክስ መስርተዋል።

በዚህ ድርጊታቸውም በአገሪቷ የመጀመሪያዎቹ ወላጆች ሳይሆኑ እንደማይቀር ተነግሯል።

በርካቶች እንደሚሉት በሕንድ ልጅ የመውለድ ጉዳይ የጥንዶች ውሳኔ ሆኖ አያውቅም።

ወላጆች፣ አማቾች፣ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ዘመድ አዝማዶች፣ ጎረቤቶች፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት አይቦዝንም። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ሙሽሪት ለሠርጓ የተቀባችው ሂና እንኳን ሳይለቅ ጥንዶቹ ልጅ እንዲኖራቸው ይወተውቷቸዋል።

የማኅበራዊ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አር ቫሳቪ "በሕንድ ጋብቻ በሁለት ጥንዶች መካከል ብቻ የሚቀር ሳይሆን ቤተሰቦችም የሚሳተፉበት፤ ያገባናል የሚሉበት ጉዳይ ነው" ይላሉ።

እኚህ ወላጆችም በልጃቸው ላይ ክስ መመስረታቸው በባህላዊ አመክንዮ የልጅ ልጅ መጠበቅ የተለመደ እንደሆነ የሚያመለክት ነው።

ወላጆቹ የልጅ ልጅ የማየት መብት እንዳላቸው ያስባሉ። ምክንያቱም በማኅበረሰቡ ውስጥ ትዳር ራስ የሚተካበት ተቋም ተደርጎ ነው የሚቆጠረው።

በመሆኑም ትዳር ከተመሰረተ በኋላ ለቤተሰብ፣ ለዘራቸው እና ለማኅበረሰቡ ሲባል ልጆችን መውለድ ይጠበቃል።

ከዚህም ባሻገር ይህ ጥያቄ ከኢኮኖሚ አንጻርም ይታሰባል። ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት እና እድገት ላይ ገንዘባቸውን ካፈሰሱ በኋላ ወደዱም ጠሉ ልጆቻቸው ባህላዊ መብታቸውን እንዲያከብሩላቸው ይፈልጋሉ።

ይህ የወላጆች ፍላጎት የልጅ ልጆችን መስጠት የልጆች ግዴታ ተደርጎ ይታሰባል።

ጋዜጠኛ ሪቱ አጋርዋል እአአ 2019 የሕንድ ቱጃር ሙኬሽ አምባኒ ለምራታቸው [ለልጃቸው ሚስት] ሺሎካ "ወራሽ ለማዘጋጀት ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ በግልጽ በመናገራቸው መነጋገሪያ ሆነው እንደነበር ትናገራለች።

"የሚቀጥለው ዓመት እኔ አያት ብቻ የምሆንበት ሳይሆን፣ አንቺም እናት ትሆኛለሽ። በዚህም እርግጠናኛ ነኝ " ሲሉ የልጅነቷን ታሪክ የሰነደው ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል። ይህ ቪዲዮውም በልደቷ ዝግጅት ላይ ተለቋል።

ከአስራ ስምንት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ግን ምራቷ፣ ሺኮላ ወንድ ልጅ መውለዷን አብስረዋል።

የሕንዱ ቱጃር ሙከሽ አምባኒ ( በስተግራ) አዲስ ተጋቢ ለሆነቸው የልጃቸው ሚስት ሺኮላ ( ከቀኝ ሁለተኛዋ) "ወራሽ ለማዘጋጀት ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ መናገራቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሕንዱ ቱጃር ሙኬሽ አምባኒ (በስተግራ) አዲስ ተጋቢ ለሆነቸው የልጃቸው ሚስት ሺኮላ (ከቀኝ ሁለተኛዋ) "ወራሽ ለማዘጋጀት ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ መናገራቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልጅ ወላጆቹን በእርጅና ዘመናቸው መንከባከብ ሞራላዊ እና ሕጋዊ ግዴታ እንደሆነ ያስቀምጣል። ይሁን እንጂ የመብት ተሟጋቾች ልጅ የመውለድ ውሳኔ የሴቷ ብቻ አይደለም ይላሉ።

በርካታ ያገቡ ሴቶችም ራሳቸውን እንዲተኩ ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው ግፊት ያልተፈለገ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በደቡባዊቷ ባንጋሎር የምትገኘውና በዚህ ታሪክ ውስጥ ሱድሃ ስንል የምንጠራት የ46 ዓመቷ የቢዝነስ ተንታኝ ወላጆቿ ሊድሯት ሲያስቡ 21 ዓመቷ የነበረ ሲሆን ገና ትምህርቷን አጠናቃ መመረቋ ነበር።

"በዝግጅቶች ላይ ቤተሰብ እና ዘመድ አዝማዶች ይጠይቁኛል። መቼ ነው አዲስ ዜና የምትነግሪን ይሉኛል። በጣም ወጣት ነበርኩ እና ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። ግን በጣም ያስፈራ ነበር። ሁልጊዜ ይህንን ጉዳይ ሲያነሱብኝ በጣም እጨነቅ ነበር" ብላለች። ይህ ከ25 ዓመታት በኋላ የሆነ ነው።

አብዛኞቹ ሴቶችም ቤተሰቦቻቸው በሚጠብቁት ነገር በመመራት በመጀመሪያው አሊያም በሁለተኛው የጋብቻቸው ዓመት ልጅ ይኖራቸዋል ትላለች ሱድሃ።

"አሁን ላይም ቢሆን የማየው ነገር አብዛኞቹ ሴቶች በተለይ ደግሞ በሕንድ ትንንሽ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ልጅ መውለድን ምንም ጥያቄ ውስጥ አያስገቡትም፤ ወዲያውኑ ልጅ ይወልዳሉ" ትላለች።

ምንም እንኳን ሕንዳውያኑ ወላጆች በልጃቸው ላይ የመሠረቱት ክስ አስደንጋጭ ቢሆንም ልጅ የመውለድ ግፊቱ አሁንም በስውር እንደቀጠለ ነው።

ልክ እንደ የአክስቷ ልጅ ስሪቲሽ [ስሟ የተቀየረ] ሁሉ የ28 ዓመቷ ሶፍትዌር ኢንጂነር በ17 ወራት የትዳር ቆይታዋ ቤተሰቦች ሰባት ስምንት ጊዜ ልጅ እንድትወልድ እንደወተወቷት ለሱድሃ ነግራታለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ አማቾቿ ይህንን ጥያቄ ሲያነሱ ትዳር ከመሰረተች ገና ስድስት ወሯ ነበር። ይሁን እንጂ በቤተሰብ አማካይነት ትዳር የመሠረቱት እርሷ እና የ30 ዓመቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው የትዳር አጋሯ በቅርቡ ልጅ የመውለድ ፍላጎት የላቸውም።

"መጀመሪያ በደንብ መተዋወቅ አለብን፣ ትኩረታችንም በሥራችን ላይ ነው" ብላለች። በመሆኑም ልጅ መውለድ የወደፊት እቅዳቸው ነው። ጥንዶች ልጅ ከመውለዳቸው በፊት ለልጁ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ እና ትኩረት ለመስጠት በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ትናገራለች።

የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ልጆች እንዲንወልድ ጠይቀውን ይህንን በተጣደፈ ሁኔታ ማድረግ እንደማንችል አስረድተናቸዋል የምትለው የ28 ዓመቷ ኢንጂነር፣ አሁንም ግን እነዚህ ጥያቄዎች እንደቀጠሉ ተናግራለች።

"ሁልጊዜ ልጅ እንድንወልድ ይነግሩናል። የሌላ ሰው ስም እየጠሩ ልጅ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህን የሚያደርጉት ለመገፋፋት ነው፤ ግን ጭንቅላቴን በመስማማት ነቅንቄ እተወዋለሁ" ብላለች።