ሩዋንዳ "በዩኬ የጥገኝነት ስምምነት ላይ በሰዎች እየነገደች አይደለም" ፕሬዚዳንት ካጋሜ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አገራቸው የዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስመልክቶ የገባችውን ስምምነት አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ሀገራቸው "በሰው ልጅ አትነግድም" ብለዋል።
በስምምነቱ መሰረት በትንንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ የተሻገሩ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ በማዛወር ጉዳያቸው በዚያ የሚታይ ይሆናል።
በሩዋንዳና በዩናይትድ ኪንግደም ተደርሷል የተባለው አወዛጋቢው የ120 ሚሊዮን ፓውንድ ስምምነት በአለም አቀፉ ዘንድ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን የሁለቱም ሀገራት ባለስልጣናት ትችት ገጥሟቸዋል።
ስምምነቱ ሲፈረም በኮንጎ ብራዛቪል፣ጃማይካ እና ባርባዶስ ጉብኝት ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ካጋሜ - ሩዋንዳ ስደተኞችን ለመቀበል በምላሹ ገንዘብ እያገኘች ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው ብለዋል።
" እኛ በሰው አንነግድም፣ እባካችሁ እርዳታ እየሰጠን ነው " በማለት ከአሜሪካው ብራውን ዩኒቨርስቲ ጋር በበይነ መረብ በነበረ ሴሚናር ላይ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ካጋሜ እንደሚሉት እንግሊዝ ሩዋንዳን የመረጠችበት ምክንያት በሊቢያ ለነበሩ ስደተኞች መጠለያ በመስጠታቸው መሆኑን ነው።
በአውሮፓውያኑ 2018 የአፍሪካ ህብረትን ሲመሩ በነበረበት ወቅት ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩና በሊቢያ መሄጃ ላጡ ስደተኞች ሃገራቸው መጠለያ እንደምትሰጥ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል።
ይህንን እርምጃም ተከትሎ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ የተወሰዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 2/3ኛ የሚሆኑት ጉዳያቸው አልቆ ወደ አውሮፓ ሀገራት እና ካናዳ አቅንተዋል።
ፕሬዚዳንት ካጋሜ አገራቸው እያደረገችው ያለችው ተግባር "የስደት ችግር ላለባቸው" እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የተሳካ ሂደት ነበር ሲሉ አወድሰዋል።
ሩዋንዳ ህገወጥ የስደተኞች ዝውውርን ለመግታት እየረዳች ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ካጋሜ ዩኬ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን የምትቀበለውን ወይም የማትቀበላቸውን ግለሰቦች ጉዳይም እልባት እስኪገኝ በሩዋንዳ እንደሚቆዩ ጠቁመዋል።
የሩዋንዳ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስምምነቱን "ከእውነታው የራቀ" ከማለት በተጨማሪ የሩዋንዳ መንግሥት "የበለጸጉ አገሮችን ሸክም" ከመፍታት ይልቅ በአካባቢው ችግሮች ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል።












