የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተገደለችው ኬንያዊት አትሌት ኃዘኑን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስለት ለተገደለችው ኬንያዊት አትሌት ዳማሪስ ሙቱዋ የተሰማውን ኃዘን ገለጸ።
ፌዴሬሽኑ በትናንትናው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ በ28 አመቷ አትሌት መገደል የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልፆ ለቤተሰቦቿ፣ ወዳጅ ዘመዶቿና አድናቂዎቿ መፅናናትን ተመኝቷል።
አትሌቷ የረዥም ርቀት ሯጮች ማዕከል በሆነችው የኬንያዋ ኢተን ከተማ ሲሆን ተገድላ የተገኘችው እስክንድር ኃይለ ማርያም የተባለ ኢትዮጵያዊ ፍቅረኛዋም ዋና ተጠርጣሪ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሙትዋን 'ጀግኒት አትሌት' ሲል ገልጿታል።
ምርመራውን የያዘው ፖሊስ ኢቴን ተብላ በምትጠራው ከተማ ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው ትውልደ ኬንያዊት አትሌት በኢትዮጵያዊ አትሌት ሳትገደል አይቀርም ብሏል።
ትውልደ ኬንያዊ እና ለባህሬን የምትሮጠው የ28 ዓመቷ ዳማሪስ ሙቱዋ በመኖሪያዋ ኢቴን ከተማ ሕይወቷ አልፎ ተገኝቷል።
ፖሊስ በአትሌቷ ግድያ ዋና ተጠርጣሪ ነው ያለውን እጮኛዋን ኢትዮጵያዊ አትሌት እየፈለገ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ግለሰቡ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም ተብሏል። ከኬንያ ወጥቶ መሰደዱም ተነግሯል።
የኬንያዋ ኢቴን ከተማ ባላት ዝነኛ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት በረዥም ርቀት ሯጮች ዘንድ ተመራጭ የመኖሪያ ከተማ ናት።
የኢቴን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ቶም ማኮሪ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ከኬንያ ከመሸሹ በፊት ሟቿ አትሌት ልምምድ በምታደርግበት ተቋም ውስጥ አብሮ ይሰለጥን ነበር ብለዋል።
"ተጠርጣሪው አብሮ ልምምድ ወደሚያደርግ ጓደኛው ደውሎ የሴት ጓደኛውን መግደሉን እና አስክሬኗ ቤት ውስጥ እንዳለ ተናግሯል" ሲሉ የፖሊስ አዛዡ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
አስክሬኗም የተገኘው መፈራረስ ከጀመረ በኋላ ነው ብለዋል።
የፖሊስ አዛዡ በወንጀሉ ተጠርጣሪ ነው የተባለው ኢትዮጵያዊ አትሌት ወደ የት አገር እንደሸሸ ያሉት ነገር የለም።
ፖሊስ የ28 ዓመቷ አትሌት ሕይወቷ ያለፈው በስለት ከተወጋች በኋላ ነው ብሏል።
አትሌቷ የተገደለችባት ኢቴን ከተማ የበርካታ አትሌቶች መኖሪያ ስትሆን ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ አግነስ ትሮፕ የተባለች አትሌት በከተማዋ በመገደሏ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።
አትሌት አግነስ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ5ሺህ ሜትር 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ ነበር።
የአግነስ ትሮፕ ባለቤት በአትሌቷ ግድያ በቁጥጥር ሥር ውሎ ይገኛል።












